ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም.

የህዝቦች የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ በዓል የሆነው ታላቁ የኢሬቻ በዓል በሰላምና በድምቀት ይከበራል!

ኢትዮጵያ ብዙ ማንነቶችን አቅፋ የያዘች አገር ናት። ህዝቦቿም የየራሳቸው መገለጫ የሆኑ ልዩ ልዩ እምነቶችና ባህሎች ያሉባት አገር እንደመሆኗ መጠን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ልዩ ልዩ ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት በይፋ የሚከበሩባት አገር ሆናለች፡፡ ወርሃ መስከረም ከገባ ወዲህ እንኳ በርከት ያሉ ልዩ ልዩ ህዝባዊ በዓላትን በሰላምና በድምቀት አስተናግዳለች፡፡

ህዝባዊ በዓላት ሁሉ መሰረታቸው ከአንድ ወይም ከሌላ ማንነት ጋር ቢያያዙም ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያስተሳስሩ የህዝቦች የጋራ በዓል ለመሆናቸው ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፡፡ የሁሉም በዓላት መገለጫ ሰላም፣ መተሳሰብና ፍቅር መሆኑንም በየበዓላቱ ያሉት አከባበሮች ያረጋግጣሉ። በውጭው ዓለም የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ ተደርገው የሚወሰዱት እነዚህ ህዝባዊ በዓሎቻችን የውጭ አገር ጎብኚዎችን ቀልብ የሚያማልሉ የገጽታችን አካል መሆናቸውም ይታወቃል፡፡ አንዳንዶቹ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገቡ ሲሆን ሌሎቹም በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለወደፊትም ቢሆን ለዓለም የምናበረክታቸው በርካታ የማይዳሰሱ ቅርሶች እንደሚኖሩን ሂደታችን ያመለክታል፡፡ እነዚህን ብርቅዬ የማይዳሰሱ ቅርሶቻችንን ሁሉ መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡

በቅርቡ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት የማይዳሰሱ ቅርሶቻችን መካከል አንዱ ሰሞኑን በሰላምና በድምቀት የተከበረው የመስቀል በዓል ነው። ሌላው በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ታላቁ የኢሬቻ በዓል ደግሞ ከፊታችን መስከረም 21 ጀምሮ በድምቀት የሚከበር ይሆናል።

መስቀልና ኢሬቻን የመሳሰሉት ህዝባዊ በዓሎቻችንን በምናስታውስበት ጊዜ በዓላቱ ከህዝቡ እምነቶች ጋር ያላቸውን ቁርኝት መገንዘብ ያሻል። ሁሉም እምነቱን እያወደሰ ምስጋና የሚያቀርብባቸው በዓላት ናቸው። በመሆኑም የበዓላቱ አከባበር ፍጹም ሰላማዊ ሁኔታን ይፈልጋል። ከሰላም ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸውና የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ መገለጫዎች ተደርገው የሚወሰዱትም ለዚሁ ነው።

በመሆኑም በቅርቡ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በህዝቡ ፍላጎትና ምኞት ልክ መከበር ይገባዋል። በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የድርሻቸውን መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡
እምነትን፣ ማመስገንና ማወደስን ዓላማ አድርገው በሚካሄዱ ሕዝባዊ በዓላት ላይ የፖለቲካ አጀንዳን ለማራመድ የሚደረግ ማንኛውም አፍራሽ እንቅስቃሴ በህዝቡ የሰላም ፍላጎት ሊመከት ይገባዋል። ሰላምን መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍላጎትና ሃላፊነት ነው። የህዝቦችን ማንነት፣ ዕምነትና ባህል በመናቅ የሚፈጸም ድርጊት እንዳይኖር በጋራ መቆም ያስፈልጋል። ከዕምነት ውጭ ያለን ፖለቲካዊ ልዩነት እና ሃሳብ ለማስተናገድ ብዙ መንገዶችና መድረኮች ያሉት ሥርዓት ገንብተናል። ሁሉንም በቦታው ማከናወን ያስፈልጋል፤ ይገባልም። የህዝቦች የዕምነት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ መገለጫ የሆኑትን የጋራ ህዝባዊ መድረኮች ማክበር ሃላፊነት ከሚሰማው ዜጋ የሚጠበቅ ነውና፣ እንደ ህዝቡ ፍላጎት ሁሉ የኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆን መንግሥት ከህዝቡ ጋር መሆኑን ያረጋግጣል፡፡