ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ነሐሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም

በዲፕሎማሲው ዘርፍ እያስመዘገብነው ያለው ድል ተጠናክሮ ይቀጥላል!
ክቡር ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ሱዳንን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባሉ ሀገሮች ውስጥ ዘወትር ለሚስተዋለው የሰላም ማጣት እና አለመረጋጋት ዋነኛው ምክንያት ድህነት ነው።

አገራችን ኢትዮጵያም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረችበት ሁኔታ ከዚህ የተለየ አልነበረም። ይሁንና ዋነኛ ጠላቷ ድህነትና ድህነት ብቻ መሆኑን በግልጽ ከለየች በኋላ መላ ሃይሏን በማስተባበር በድህነት ላይ በከፈተችው መጠነ ሰፊ ትግል እነሆ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ ጠላቷን በማንበርከክ ላይ ትገኛለች። ይህ ውስጣዊ ጥንካሬዋም በውጭው ዓለም ዘንድ ከድህነት ጋር ለዘመናት ተቆራኝቶ የነበረውን ገጽታዋን በመቀየር ዛሬ የምትታወቀው ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ እንዲሆን አስችሏታል።

ከዚሁ በተጓዳኝ በውጪው ዓለም በዲፕሎማቲክ ዘርፍ እየሰራናቸው ያሉ ተመጋጋቢ ሥራዎችም ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በማጎልበት ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። በተለይም እየተገባደደ ባለው ዓመት ያካሄድናቸውን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራዎቻችንን ካየን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያገኘነው ትብብርና ድጋፍ ከፍተኛ ነበር። በአገራችን በንግድና በኢንቨስትመንት እየተመዘገበ ያለው ዕድገትም ለዚህ አመላካች ነው።

በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ፋይዳ በአገራችን ለዘመናት ሥር ሰዶ የኖረውን አስከፊ ድህነት ከመሰረቱ በማጥፋት የህዝቦቻችንን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታችንን ማፋጠን ነው። በመሆኑም ከአካባቢያችን አገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በማራመድ አካባቢያችንን የሰላም ቀጠና ለማድረግና ከአገሮቹም ጋር ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን አከናውነናል፤ እያከናወንንም እንገኛለን።

በዚህ ረገድ ከጎረቤት አገራት ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጋር በመሰረተ ልማት ማስፋፋት፣ በሃይል አቅርቦት፣ በንግድ፣ በትምህርት ዕድል ወዘተ በመሳሰሉት አህጉራዊ ትስስር ለመፍጠር ያካሄድናቸውን ጥረቶች መጥቀስ ይቻላል።

በአጠቃላይ የውስጥ ጥንካሬያችንን ለማጎልበት ትኩረት ሰጥተን የሰራነው ሥራ የውጭ ሥራችንን በማፋጠንና ገጽታችንን በመቀየር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከዚህ በመነሳትም በውጭ ግንኙነታችን ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያችን ትኩረት ሰጥተን በሰራናቸው ሥራዎች የተገኘው ውጤት የአገራችንን ገጽታ በመለወጥ ረገድ ጉልህ ሚና ከመጫወቱም ባሻገር ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተሰሚነታችንንና ተጽዕኖ ፈጣሪነታችንን እያሳደገው መምጣቱ እሙን ነው።

በመሆኑም በያዝነው ዓመት በዲፕሎማሲው መስክ ያስመዘገብናቸውን ትላልቅ ድሎች አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል። በዚህ አጋጣሚ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተሰሚነት ያላት፣ በኢኮኖሚ የበለፀገች እና ህዳሴዋን ያረጋገጠች አገር ለመፍጠር እየተካሄደ ባለው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።