ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም

አህጉራዊ ተቀባይነታችንን ያጎለበቱልንን እሴቶቻችንና ውስጣዊ ጥንካሬያችንን ለማስቀጠል በጋራ ልንረባረብ ይገባል!
ከአፍሪካ ኅብረት መስራች አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትታወቀው ውድ አገራችን ኢትዮጵያ 30ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ፣ ከወዲሁ ቅድመ ጉባኤ ስብሰባዎችን ማስተናገድ ጀምራለች።

ከ40 በላይ የሚሆኑ አገራት መሪዎች እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው የታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች የሚታደሙበትን ይህንን ግዙፍ አህጉራዊ ጉባዔ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አገራችን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ በአፍሪካ መሪዎች የተወሰነው፣ አገራችን አኩሪ የነጻነት ታሪክ ባለቤት፣ ተነጻጻሪ ሰላም ያላት፣ እንግዳ ተቀባይና የሁሉም አፍሪካውያን ኩራት፣ እና በማንኛውም ወቅት ዕምነት የሚጣልባት በመሆኗ ነው፡፡

ይህ የሚያሳየው፣ በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች ብቅ ጥልቅ እያለ የሚታየው ጊዜያዊ ቀውስ አጠቃላዩን የአገራችንን ገጽታ ሊወክል እንደማይችል በአፍሪካውያኑ ዘንድ የተያዘውን ግልጽ አቋም ነው፡፡
ለዘላቂ ሰላም እና ለፈጣን እድገት አስተማማኝ የሆነ መሠረት በአገራችን መጣሉን፣ በዚህም አገራችን ከራሷ አልፋ ለአፍሪካውያን ሰላም መከበር እና ለሁለንተናዊ ዕድገታቸው መረጋገጥ ኢትዮጵያ እየተጫወተችው ያለውን ጉልህ ሚና በመገምገም የተደረሰበት አቋም መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። በዚህ ላይ፣ የህዝባችን ሰላም ወዳድነት እና የእንግዳ ተቀባይነት ባህል እንዲሁም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታሪክ ያላት ቦታም የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳበረከቱም ይታወቃል።

በአጭር አገላለጽ አፍሪካውያን ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚሰጡት ክብር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን መገንዘብ ያሻል።

በመሆኑም፣ እኛም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰጠን ክብር ልክ መልካም ሥማችንንና ክብራችንን ጠብቀን እና አጠናክረን መቀጠል ይገባናል። እስካሁን ካለፍንበት ሂደት ማረጋገጥ የቻልነው፣ ዛሬ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የአገራችን ተሰሚነት እየጨመረ የመጣው ውጫዊ ገጽታችንን ለማሳመር ብለን በሠራነው ሳይሆን ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በተጨባጭ ማሳዬት በመቻላችን ነው።

አሁንም መፈታት ያለባቸው የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩብንም፣ ዘላቂ ሰላምን ከማስፈን፣ ፈጣን እና ተከታታይ ዕድገትን ከማምጣትና አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከመገንባት አንጻር ላለፉት ዓመታት የሄድንበትን ጉዞ አጠናክረን መቀጠል ይገባናል። ያሉብንን ይሁን ወደፊትም የሚያጋጥሙንን ችግሮች ሁሉ በዴሞክራሲ ባህል፣ በሠለጠነ እና በምክንያታዊ አስተሳሰብ ላይ ተመስርተን በውይይት እየፈታን መሄድ ይገባናል፡፡

በተጨማሪም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ልዩ አድናቆት ያተረፉልንን የእንግዳ ተቀባይነት፣ የመቻቻልና የመደጋገፍ የመሳሰሉ እጹብ ድንቅ እሴቶቻችንም አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡

በዚህ አጋጣሚ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ተሠማርተው የሚገኙና ለእንግዶቻችን አገልግሎት የሚሰጡ የግል ባለሃብቶቻችን፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ሰራተኞቻቸው፣ ለውጭ እንግዶቻችን የሚሰጡት መስተንግዶ በተለመደው ኢትዮጵያዊ መልካምነት የታጀበ መሆን ይገባዋል፡፡

በተለይም እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ ተቋም፣ ብሎም እንደ አገር ከጉባኤ አስተናጋጅነታችን በዘላቂነት እያገኘናቸው ያሉ ጥቅሞችን የሚሸረሽሩ ተግባራትን በመከላከል ረገድ መላው ህዝባችንና በተለይም ባለሃብቶቻችን አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

መላው ህዝባችን ለአህጉራዊው የመሪዎች ጉባኤ መሳካት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ፣ ብሎም አህጉራዊ ተቀባይነታችንን ያሳደገልንን ውስጣዊ ጥንካሬያችንን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል።