ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ -የካቲት16 ቀን 2010 ዓ.ም

እድገታችንን ለማፋጠንና ችግሮቻችንን ለመፍታት፣ በቅድሚያ ሰላማችንን የማረጋገጥ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል!

የብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ መኖሪያ፣ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤትና የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት የሆነችው ውድ አገራችን ኢትዮጵያ፣ለዘመናት ነጻነቷን ጠብቃ መኖር የቻለችው ጀግኖች ልጆቿ በየጊዜው የመጣባቸውን ወራሪ ሃይል በጋራ እየተጋፈጡ በከፈሉት መስዋዕትነትና ባስመዘገቡት ድል ነው።

የጋራ ጠላት በመጣባቸው ወቅት ሁሉ የውስጥ ችግሮቻቸውን ወደጎን በማድረግ በአንድነት ተሳስረው ጠላትን ሲጋፈጡ እንደኖሩ ከሚያረጋግጡልን ታሪካዊ ሁነቶች መካከል የፊታችን የካቲት 23 የሚከበረው የአድዋው ድል ተጠቃሽ ነው።

የቀደመው ትውልድ ለአገሩና ለወገኑ ይህን መሰሉን አንጸባራቂ ታሪክ ሰርቶ እንዳለፈው ሁሉ፣የአሁኑም ትውልድ የወቅቱ ጠላት በሆነው ድህነት ላይ በአንድነት ተሰልፎ መጠነ ሰፊ ጦርነት በመክፈት የራሱን ወርቃማ ታሪክ እየጻፈ ይገኛል።

የአሁኑ ትውልድ ፍላጎት በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲኖር፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እና ፈጣንና ፍትሃዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲመጣ ነው። ይህንንም የአገራችን ህዝቦች የጋራ ቃልኪዳን ሰነድ በሆነው የኢፌዴሪ ህገመንግስት ላይ በግልጽ ያረጋገጠው ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ህገመንግሥቱ ባጎናጸፏቸው መብቶች፣የሀገራቸው ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውና እኩልነታቸው ተረጋግጦላቸው፣ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ልማታቸውን ማፋጠን ችለዋል። በአገራችንም አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ቆይቷል፡፡

በዚህ የተነሳም፣ ምንም እንኳን አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ የስጋት ቀጣና ሆኖ መቆየቱ ቢታወቅም በተነጻጻሪ የተረጋጋ ሰላም ያላት፣ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ እና ምቹና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ችላለች። ከራሷ አልፋ ለሌሎች አገራትም የሰላም ሃዋርያ ለመሆን በቅታለች።

በውስጣችን የፈጠርነው ሰላምና መረጋጋት፣ ለምንመኘው ፈጣን ዕድገት ምቹ መሰረት ስለጣለልንም አገራችንን ወደከፍታ ያወጡ በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ ችለናል። በቅርቡ ታሪካችን እንዳረጋገጥነው፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስከፊ ድርቅ አጋጥሞን በነበረበት ወቅት ድርቁ ወደ ረሃብ አደጋነት ሳይቀየር በራሳችን አቅም ለመቋቋም መቻላችን ለሌሎች አገራት በተሞክሮነት እየተላለፈ ያለ ስኬት ነው።

ትውልዱ አሳፋሪውን የተረጅነት ታሪኩን ማስቀረት የቻለው በግብርናና በመሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ ባስመዘገበው ስኬት ይሁን እንጂ መሰረቱ ሰላም ነው።

ባለፉት ዓመታት ትውልዱ እያስመዘገባቸው የመጡ በርካታ ድሎች እንደነበሩት ሁሉ ግን በሂደቱ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችም ነበሩ፤ አሁንም በርካታ ችግሮ ችአሉ።

ዕድገታችንን ተከትለው በየጊዜው የመጡም ልዩ ልዩ የህዝብ ፍላጎቶች እንደዚሁ አጋጥመውናል።ይሁን እንጅ እድገታችንን ለማስቀጠልና ብሎም ለማፋጠን፣ እንዲሁም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ህዝባችንን እያማረሩ ያሉትን ችግሮችና ጊዜ ያመጣቸውን የህዝቦች የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በቅድሚያ ሰላማችንን አስተማማኝ ማድረግ ይጠይቀናል።

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መፋጠን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በአገራችን የዴሞክራሲ ባህል እየጎለበተ እንዲሄድ ለማስቻል የሰላም መኖር ወሳኝነቱ አጠያያቂ አይደለም።

ከዚህ አንጻር፣ ቀዳሚው ጉዳይ መላው ህዝባችን እንደተለመደው የየአካባቢውን ሰላም በባለቤትነት ስሜት መጠበቅ ይገባዋል።

በተለይም የዚች አገር የለውጥ ሃይል የሆኑት ወጣቶቻችን የአገራችንን ሰላም አስተማማኝ ከማድረግ አንጻር የራሳቸውን ዓይነተኛ ሚና ሊጫዎቱ ይገባል።

ወጣቶቻችን የሚጠይቋቸውን መብቶች ለማረጋገጥ የሚቻለው በቅድሚያ የአገራችን ሰላም አስተማማኝ መሆን ሲችል ብቻ መሆኑን ተገንዝበው በያካባቢያቸው ግንባር ቀደም የሰላም ዘብ ሆነው እንዲሰለፉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

የዜጎችን ጥያቄዎች ለመመለስና መብቶችንም ለማስከበር የሚቻለው የሁሉ ነገር መሠረት የሆነውን ሠላም ስናሰፍን በመሆኑ ሁሉም አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።