ዜና ዜና

ከአማራ ክልል ለውጭ ገበያ ከተላከ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ሽያጭ ከ154 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

በአማራ ክልል ወደ ውጭ ሃገራት ከተላኩ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች ከ154 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

 የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አፈወርቅ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ምርቶቹ የተላኩት በ2010 የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ነው፡፡

 ከተገኘው ገቢ ውስጥ 142 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላሩ ከሰሊጥ፣ ቦለቄ፣ ጥራጥሬና መሰል የግብርና ምርቶች የተገኘ ነው።

 ለገበያ ከቀረበው 1ሺህ ቶን አበባ ሽያጭ ደገሞ  ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል ።

 ቀሪው ጨርቃ ጨርቅን ጨምሮ ከሌሎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ሽያጭ የተገኘ መሆኑን ሀላፊው ተናግረዋል ።

 "ከኢንዱስትሪና ከእንስሳት የተገኘው ገቢ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም " ያሉት ሀላፊው  ወደፊት የላኪዎችን አቅም በማጎልበት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢም የእቅዱን 89 ነጥብ 1 በመቶ ያሳካ መሆኑን ጠቁመዋል ።

 "ይሁንና የግማሽ ዓመቱ የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ በ2009 ሙሉ በጀት አመት ከተገኘው በ22 ሚሊዮን ዶላር ብቻ የሚያንስ በመሆኑ በዘርፉ የተሻለ እድገት ተመዝገቧል " ብለዋል ።

 ለዚህም በዚህ ዓመት የተሻለ የሰሊጥ ምርት መገኘቱ፣ በዓለም አቀፍ ያለው የገበያ ዋጋ የተሻለ በመሆኑና ቦለቄ ወደ ውጭ ንግድ እንዲገባ በመደረጉ ነው ብለዋል።

 እንዲሁም ባለፈው ዓመት እጅግ አነስተኛ የነበረው የእንስሳት ንግድ በዚህ ዓመት ከላኪዎች ጋር በተደረገው ውይይት ወደ መላክ መግባታቸው እንደሆነም አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል።

 በግብርና  ምርቶች የንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ሀይለማርያም መለሰ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ስድስት ወራት ከ5 ሺህ ኩንታል በላይ ባቄላ በመተማ በኩል ለሱዳን ገበያ አቅርበዋል ።

 በወራቶቹ ውስጥ 6ሺህ ኩንታል ባቄላና 3ሺህ ኩንታል ግብጦ በመተማ በኩል ለሱዳን ገበያ ማቅረባቸውን የገለፁት ደግሞ አቶ ሀሰን መልኬ ናቸው።

 ተወዳዳሪ የግብርና ምርቶችን በጥራትና በብዛት በመላክ በኩል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 በንግድ ሚኒስቴር የወጪ ምርቶች ጥራት ፍተሻና ቁጥጥር ስራ አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ መሆኑን የገለፁት ባለሀብቶቹ መተማ ላይ ቅርንጫፍ ቢከፈት የወጪ ምርት ግብይቱን የበለጠ እንደሚያቀላጥፈው ጠቁመዋል ። 

እስከ በጀት አመቱ መጨረሻ ከክልሉ ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች ሽያጭ  ከ347 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ታውቋል ።

ባህርዳር  መጋቢት 4/2010  /ኢዜአ