ዜና ዜና

ሆስፒታሉ ለ150 የጎዳና ተዳዳሪዎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት ሰጠ

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከአራዳ ኬር ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በመዲናዋ ለሚገኙ 150 የጎዳና ተዳዳሪዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሰጠ።

 ሆስፒታሉ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

 የህክምና አገልግሎቱን ሲሰጡ ያገኘናቸው ዶክተር ሰለሞን ደሳለኝ እንደገለጹት የጎዳና ተዳዳሪዎች ባሉባቸው የኢኮኖሚና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ሳቢያ ሕክምና አያገኙም።

 በመሆኑም ካሉባቸው የጤና ችግሮች እንዲፈወሱ ሆስፒታሉ ተከታታይ ህክምና ማግኘት የሚያስችላቸውን ስርዓት በመዘርጋት ሙሉ የህክምና አገልግሎት እየሰጣቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

 አራዳ ኬር ፋውንዴሽን የምገባና የአልባሳት ድጋፍ ሲያደርግላቸው ቆይቷል ያሉት ዶክተር ሰለሞን ሆስፒታሉ ደግሞ ለምን ነጻ ሕክምና አያደርግም በሚል ተነሳሽነት አገልግሎቱን መጀመሩን ተናግረዋል።

 የአራዳ ኬር ፋውንዴሽን መስራች አቶ ሄኖክ ዓብይ ነጻ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለመደገፍ በማሰብ ከአራት ዓመታት በፊት ማሕበሩን መመስረታቸውን ገልፀዋል።

 ፋውንዴሽኑ ከሆስፒታሉ ጋር በመተባበር ሕክምና እንዲያገኙ ሲያደርግ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንና ከዚህ ቀደም የመመገብና ልብስ የማልበስ ተግባራትን ያከናውን እንደነበር ጠቅሰዋል።

 በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ፕሮግራሙ አስተባባሪ ወይዘሮ ቅድስት ተስፋዬ ለጎዳና ልጆች ምግብና አልባሳት ከመስጠት ባለፈ ጤንነታቸውን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

 በእስካሁን ሂደት የቆዳና የጉበት በሽታዎች በአብዛኞቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ የሚስተዋሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

 በቀጣይም ከመንግስት ጋር በመስራት መማር የሚፈልጉ እንዲማሩ፤መስራት የሚሹም እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።

 የጎዳና ተዳዳሪዎችም የተደረገላቸው ሕክምና በቀጣይ የተስተካከለ ሕይወት እንዲኖሩ ተስፋ እንደሰጣቸው ገልጸው ዕድሉን ያላገኙትም ህክምና የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

ሚያዝያ 7/2010/ኢዜአ