ዜና ዜና

በጋምቤላ ክልል ከ134 ሺህ ለሚበልጡ ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት ሊሰጥ ነው

በጋምቤላ ክልል ከ134 ሺህ ለሚበልጡ ህፃናት የፖሊዮ ክትባትና የቫይታሚን "ኤ" እንክብል ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የጤና ማበልጸግና የበሽታ መከላከል ወሳኝ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሪያንግ ፖች ለኢዜአ እንደገለጹት አገልገሎቱ የሚሰጠው ስድስት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ጨምሮ በክልሉ በሚገኙ 13 ወረዳዎችና በጋምቤላ ከተማ ነው።

ከነሐሴ 12 ቀን 2009 ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ዘመቻ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ከ134 ሺህ በላይ ህፃናት የፖሊዮ ክትባት እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

"እድሚያቸው በስድስት ወራትና በአምስት ዓመት መካከል ለሚገኙ ከ89 ሺህ ለሚበልጡ ህፃናት ደግሞ ተጨማሪ የቫይታሚን ''ኤ'' እንክብል ይሰጣቸዋል "ብለዋል።

በሁለትና በአምስት ዓመት የእድሜ ክልል 70 ሺህ 879 ህፃናት ከፖሊዮ ክትባትና ከቫታሚን'' ኤ'' እንክብል በተጨማሪ የሆድ ጥገኛ ተህዋሲያን ህክምና እንደሚሰጣቸውም አመልክተዋል።

በዘመቻው ከ89 ሺህ በሚበልጡ ህፃናትና በ21 ሺህ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች ላይ ከሚከናወነው የምግብ እጥረት ምርመራና ልየታ በተጨማሪ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ያላባቸው ህፃናት ምዝገባ እንደሚካሔድም አስረድተዋል።

የቫይታሚን ''ኤ'' እንክብል እደላና የሆድ ጥገኛ ተህዋሲያን የህክምና አገልግሎት በጊዜያዊነት በተቋቋሙ 293 ጣቢያዎች የሚሰጥ ሲሆን የፖሊዮ ክትባቱ ቤት ለቤት የሚከናወን ነው።

ከአንድ ሺህ 465 በላይ የጤና ባለሙያዎችና በጎ ፍቃደኞች ለሚሰማሩበት ለዚህ ዘመቻ ማስፈጸሚያ በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅትና የዓለም ጤና ድርጅት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደባቸውን አስታውቀዋል።

በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሚሆኑት ከ134 ሺህ በላይ ህጻናት መካከል መካከል 67 ሺህ 960 የሚሆኑት በስድስቱ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ህፃናት መሆናቸውን ከክልሉ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ጋምቤላ ነሀሴ 6/2009/ኢዜአ/