ዜና ዜና

በደቡብ ክልል 133 ሚሊዮን ብር የመንግስት ገንዘብ ከብክነት ማዳን ተቻለ

በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመረያዎቹ ስድስት ወራት 133 ሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳን መቻሉን የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የበጀት አመዳደብና የወጭ ቅነሳ መመሪያ መዘጋጀቱም ተመልክቷል፡፡ 

የቢሮው ኃላፊ አቶ ታምራት ዲላ ትናንት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት መስሪያ ቤታቸው በ2009 በጀት ዓመት የመስተንግዶ ወጪ ለመቀነስ ያዘጋጀው መመሪያ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት መመሪያው ተግባራዊ በማድረግ ባለፉት ስድስት ወራት ለመስተንግዶ አለአግባብ  ይባክን የነበረን 133 ሚሊዮን ብር ከብክነት ማዳን መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በየዓመቱ ይመደብ የነበረው የመስተንግዶ ወጭ ከ177 ሚሊዮን ብር ወደ 45 ሚሊዮን ብር ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡

ቢሮው ቁጠባን መሰረት በማድረግ ሃብትን ከብክነት የሚያድንና የፋይናንስ አሰራር ግልፅ የሚያደርግ የበጀት አመዳደብና የወጭ ቅነሳ መመሪያ ማዘጋጀቱም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

መመሪያው ሃብትን ከብክነት ማዳን፣ የፋይናንስ አሰራር ውጤታማና ወጪዎች እሴት ጨማሪ እንዲሆኑ ማድረግ ዓላማው ያደረገ ነው፡፡

ይህም የመደበኛና ካፒታል በጀት የሚመደበብትን አሰራር ፣ በአላቂ እቃዎች፣ በነዳጅና ዘይት፣ በህትመት፣ በተሸከሪካሪዎች ጥገና የሚወጡ ወጪዎችና በቋሚ ንብረት ግዥ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል፡፡

"የአልባሳት፣ የቲ-ሸርት፣ የባርኔጣ፣ አልግባብ የሚታተሙ ባነሮች፣ ያለዕቅድ ታትሙው በየቦታው የሚጣሉ መጽሔቶች  ህትመትና በማስታወቂያ ወጪዎችም ላይ ገደብ ለማበጀት የሚረዳ መመሪያ ነው" ብለዋል ኃላፊው፡፡

ከተሸከሪካሪዎች ወጪ ቀጥሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሃብት የሚባከነው በግንባታ ቁሳቁሶችና  በማሽኖች ኪራይ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ታምራት  "ከአሁን በኋላ ይህም ቢሆን በመመሪያው መሰረት እንዲሆን ያዛል" ብለዋል፡፡

መመሪያው በቂ ቅድመ ዝግጀት ላልተደረገበት ግንባታ  በጀት መፍቀድ፣  የግንባታ ውልና አስተዳደር ክፍተት ለማስተካከልም  ያግዛል ተብሏል፡፡ 

የስልክ ወጪ፣ የውጭ ጉዞ ስምሪትና ስልጠናዎች ጠቀሜታቸው ተገምግሞ ከታመነበት ብቻ እንደሚፈቀድም ተመልክቷል፡፡

ጥር 3/2010፤ኢዜአ