ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ታህሳስ 13 ቀን 2010 ዓ.ም

መሠረታዊ ችግሮቻችንን በተግባር ለመፍታት የሚያስችለንን የጋራ አቅም ለመፍጠር እንረባረብ!

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጀምሮ፣ ሕዝባችንን ክፉኛ እያማረሩ ያሉትን የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ለመፍታት፣ እንዲሁም ከልማት ጋር ተያይዘው የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ እና በአንዳንድ አካባቢዎች እያጋጠሙን ያሉትን ቀውሶች በተግባር ለመፍታት የሚያስችል የጋራ አቅም ለመፍጠር መንግስትና መሪው ድርጅት የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክረው በቀጠሉበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡

መፈታት ያለባቸው ልዩ ልዩ ችግሮች ከፊታችን ተጋርጠው ባሉበት በአሁኑ ወቅት ላይ ሆነን እንኳ ዓለምን ያስደነቀ ፈጣን፣ ተከታታይ እና ፍትሃዊ ዕድገት ማስመዝገባችንን ግን አላቆምንም።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በየጊዜው የሚያጋጥሙንን ልዩ ልዩ ችግሮች ሁሉ በሳይንሳዊ መንገድ በመለየትና ከህዝባችን ጋር ሆነን በመፍታት ረገድ የካበተ ልምድ ማዳበራችንም ሌላው ሊሰመርበት የሚገባ ታላቅ ዕውነታ ነው።

ከዚህ በመነሳትም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠሙንን መሠረታዊ ችግሮች በተግባራዊ እርምጃዎች ለመፍታት የሚያስችለንን የጋራ አቅም ለመፍጠር እየተረባረብን ባለንበት በአሁኑ ወቅት ላይ ሆነን ስለመጪው ጊዜ ብሩህነት ከወዲሁ በእርግጠኝነት ለመናገር እንችላለን።
የመንግሥትና የመሪ ድርጅቱ አመራሮች አሉብን የሚሏቸውን ድክመቶች ሁሉ አንድ በአንድ ለመፍታት ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ ባሉበት በዚህ ወቅት ላይ፣ መላው ሕዝባችንም የችግሮቹ መፍቻ ዋነኛ አቅም እንደመሆኑ መጠን የተለመደውን የግንባር ቀደምትነት ሚናውን ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ መጫወት ይጠበቅበታል፡፡
የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶቻችን በበኩላቸው፣ ከመሠረታዊ የዕድገት ጎዳናችን የሚያስቱንን ጉዳዮች በውል ማጤን፣ እያንዳንዱን ውሳኔያቸውንም እንደ ግለሰብና ቤተሰብ፣ እንደ አገር እና ህዝብም በዘላቂ ጥቅም ላይ የሚኖረውን እንድምታ ከግምት ያስገባ፣ በአጠቃላይ በምክንያታዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
ልማታችንንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችንን በምንፈልገው ፍጥነት ማሳካት የምንችለው፣ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰላማችን ዘላቂና አስተማማኝ ሆኖ ሲቀጥል ብቻ መሆኑን በጥብቅ መገንዘብ ያሻል።
በመሆኑም መላው ሕዝባችን ለዘመናት የዘለቁትን አብሮ የመኖር፣ የመቻቻል፣ የመተሳሰብና ችግሮችን በጋራ የመፍታት አኩሪ ባህሎችና እሴቶች ይበልጥ በማዳበር አሁን ያጋጠሙንን መሠረታዊ ችግሮች በተግባራዊ እርምጃዎች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት እንደወትሮው ሁሉ ዋነኛ አቅም ሆኖ የባለቤትነት ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡