ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ሚያዚያ 13 ቀን 2009 ዓ.ም

የዴሞክራሲ ተቋሞቻችን ለጥልቅ ተሃድሶው መሳካት ድርሻቸውን እየተወጡ ነው!
ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት አገራችንን ወደፊት በማራመድ ውጤታማ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ከእነኚህ ተግባራት የተገኙ መልካም ልምዶቻችንን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና በሂደቱ ያጋጠሙንን ድክመቶች ለማረም ይቻል ዘንድም የኢፌዴሪ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሲቪል ሰርቪሱን፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ የሲቪክ ማህበራትንና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የተሃድሶ እንቅስቃሴያችን ዋና ዓላማ በሕዝብ ተሳትፎና ባለቤትነት የተለኮሰውን የአገራችንን የሕዳሴ ጉዞ ይበልጥ በጥራት ማፋጠን ነው። ከዚህ አንጻር በተከናወኑ ተግባራትም ተሃድሶን በማጥለቅ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች ደረጃ በደረጃ እየመጡ ይገኛል።

ለመልካም አስተዳደር ማስፈን ባለው ሚና የመንግሥት ተቋማት ከሠራተኞቻቸው ጋር በጥልቀት ተወያይተው ለለውጥ ራሳቸውን ዝግጁ እያደረጉ ነው። ዴሞክራሲን ለማጥለቅ እንዲያግዝም በገዢው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ውይይት ተጀምሯል።

የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ተቋማትም ህዝብን በስፋት ከማገልገል አንጻር ራሳቸውን ለማሻሻል የሚያስችሏቸው ተግባራት እያከናወኑ ይገኛሉ።መንግስታዊ ስርዓቱ ራሱን በራሱ ማረም እንዲችል ነጻ ሆነው የተቋቋሙት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የመሰሉ የዲሞክራሲ ተቋማትም የተጣለባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ይገኛል፡፡

በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደቡብ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያካሄደውን ምርመራ ውጤትና ምክረ ሃሳብ ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡም የዚህ አካል ነው፡፡ ምክር ቤቱ ይህንኑ የምርመራ ውጤትና ምክረ ሀሳብ ሲመረምር ቆይቶ መቀበሉና ውሳኔዎች ማስተላለፉም ተሃድሶው በሚፈለገው ልክ እየጠለቀ የመሄዱ ማሳያ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት እነኚህን የመሠሉ ተግባራት ጥልቅ ተሃድሶውን ወደላቀ ተግባር ለማሸጋገር የሚያግዙ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩ ያምናል፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማቱ የጀመሯቸው ሥራዎች የተሃድሶ እንቅስቀሴውን በማገዝ የኢፌዴሪ መንግሥት ለህግ የበላይነት መከበር እና ለዜጎቹ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ መጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳኩ ናቸው፡፡

የጥልቅ ተሃድሶው አንዱ ዓላማ የዴሞክራሲ እና የቁጥጥር ተቋሞቻችን እንዲጎለብቱና መንግስት ራሱን በራሱ የማረም አቅሙን እንዲያሳድግ ማድረግ እንደመሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማቱ ይህን መሰል እንቅስቃሴ ሊበረታታ የሚገባው ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት፡ የዜጎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱና የህግ የበላይነት ይበልጥ እንዲረጋገጥ፡ የዴሞክራሲ ተቋማት በጥልቅ ተሃድሶው የተገኙትን ምቹ ሁኔታዎች ለማገዝ የሚጫወቱት ሚና ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያስተላልፋል።