ዜና ዜና

በኦማን የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የነበሩ 134 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

ኦማን የሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ በሀገሪቱ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ታስረው የነበሩ 134 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

ኤምባሲው ከኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ባደረገው ጥረት ኢትዮጵያውያኑ ከእስር ተፈትተው ከመስከረም 21 እስከ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በሶስት ዙር ወደ ሀገራቸው በሰላም ተመልሰዋል።

በእስር ላይ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት የጉዞ ሰነድ ስላልነበራቸው እና በራሳቸዉ ወጭ የጉዞ ሰነድ ለማዉጣት የማይችሉ በመሆኑ ኤምባሲዉ በያሉበት ማረሚያ ቤት በመንቀሳቀስ የአንድ ጊዜ የጉዞ ሰነድ (laissez-passer) በነጻ እንዲሰጣቸዉ አድርጓል።

ከእስር የተፈቱት ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው ኤምባሲው ላደረገው ድጋፍ እና ጥረት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በተለያዩ የልማት መስኮች ላይ በመሳተፍ ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን ለማገልገል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በኦማን የሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብት ለማስከበር ከኦማን መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያሳያል።

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)