ዜና ዜና

ለግድቡ ግንባታ ከመዲናዋ ነዋሪዎች 126 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የከተማዋ ከንቲባ ገለጹ።

ከንቲባ ድሪባ ኩማ የአዲስ አበባን የ2009 ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለከተማዋ ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደገለፁት አስተዳደሩ ለግድቡ ግንባታ 150 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከ126 ሚሊዮን በላይ ብር ሰብስቧል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከከተማዋ ነዋሪዎች ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው የግሉን ባለሃብት እንደማይጨምር አስታውቀዋል።

የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን ለማድረግ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከመላው አገሪቱ ከዘጠኝ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል።

አዲስ አበባ ሀምሌ 3/2009/ ኢዜአ/