ዜና ዜና

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 120 ሜጋ ዋት የነፋስ ሀይል ማመንጫ ሊገነባ ነው

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 120ሜጋ ዋት የነፋስ ሀይል ማመንጫ ሊገነባ መሆኑን የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዥንዋ እንዳስታወቁት ግንባታው በሃምሌ ወር ይጀመራል፡፡

ፕሮጀክቱ ዶንግፋንግ በተሰኘው የቻይና ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን እንደሚገነባ ተነግሯል፡፡

በ257 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የሚገነባው ፕሮጀክቱ በ18 ወራት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

የፕሮጀክቱ ወጭ 85 በመቶው በቻይና ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ የሚሸፈን ሲሆን 15 በመቶው በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፈን በዘገባው ተመልክቷል፡፡

በአገሪቱ ከዚህ ቀደም በአሸጎዳ 120 ፣ በአዳማ I 51 እና በአዳማ II 153 ሜጋ ዋት የሀይል ማመንጫዎች መገንባታቸው ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ እአአ እስከ 2020 ከውሃ ፣ከነፋስ፣ ከፀሃይና ከሌሎችም ምንጮች በመጠቀም የሃይል መጠኗን ወደ 17,300 ሜጋ ዋት ለማሳደግ አቅዳ እየሰራች እንደሆነም ዘገባው አስታውሷል፡፡

ግንቦት 10/2009/ኢዜአ/