ዜና ዜና

ዶክተር መረራ ጉዲናን ጨምሮ 115 እስረኞች ተለቀቁ

ዶክተር መረራ ጉዲናን ጨምሮ 115 እስረኞች ዛሬ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተለቀቁ።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ አገሪቷን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ የፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህም የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ የ528 ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

የክስ መቋረጥ ሂደቱን ተከትሎም ዛሬ ዶክተር መረራ ጉዲናና ዶክተር ሩፋኤል ዲሳሳን ጨምሮ 115 እስረኞች ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተለቀቁ ሲሆን አምስቱ ሴቶች ናቸው።

የተቋቋመው ግብረ ኃይል በፍትህ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ በመንደፍ እየሰራ መሆኑን ባለፈው ሣምንት መግለጹ ይታወሳል።

ጥር 9/2010 /ኢዜአ/