ዜና ዜና

ባለፉት 10 ወራት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ከ651 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ከ651 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡

የባለስልጣኑ የኮምዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ሳህለማርያም ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት ለውጭ ገበያ ከቀረቡት ምርቶች መካከል የቡና ምርት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡

በዚሁ ጊዜ ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ ካቀረበችው 185 ሺህ 241 ቶን ቡና ከ651 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ነው ባለሙያው ያብራሩት፡፡

ባለስልጣኑ ባለፉት 10 ወራት ከ225 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ አቅርቦ ከ9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት እቅድ ይዞ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በዓለም ዓቀፉ የቡና ገበያ መዋዠቅ ምክንያት ባለፉት 10 ወራት በአቅርቦት ደረጃ ማሳካት የተቻለው የእቅዱን 82 በመቶ ያህል ሲሆን በገቢ ደረጃ ደግሞ የእቅዱን 71 በመቶ መሆኑን ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

በቀጣዮቹ ሁለት ወራት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከማቸው ቡና ወጥቶ ለገበያ ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡

የይርጋ ጨፌ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ማሞ እንዳሉት ዩንየኑ በዘንድሮው የምርት ዘመን ሁለት ሺህ 268 ቶን ቡና ወደውጭ ለመላክ ቢያቅድም እስካሁን መላክ የቻለው 36 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው፡፡

ዩንየኑ በጀቱን ያሚጠናቅቀው እስከ ጳጉሜ አምስት መሆኑን ያብራሩት አቶ ታከለ እቅዱን በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለማሳካት እርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የአማሮን ቡና ለውጭ የሚልከው የአማሮ ጋዮ ቡና ባለቤት ወይዘሮ አስናቀች ቶማስ በበኩላቸው በዘንድሮው አመት አስር ኮንቴነር ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ድርጅታቸው አርሶ አደሩ ጥራት ያለው ቡና እንዲያቀርብ በማድረግ በኩል ስልጠና በመስጠትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ለጥራቱ መሻሻል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ባለፉት አስር ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ከስምንት ሺህ 761 ቶን በላይ የሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ከ167 ሺህ ቶን በላይ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ከ571 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ባለስልጣኑ ትናንት በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የ3ኛው ሩብ ዓመት ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ግንቦት 8/2010/ኢዜአ/