ዜና ዜና

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከህብረተሰቡ የተሰበሰበው ገንዘብ 10 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ደርሷል፡፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከህብረተሰቡ በተለያየ መንገድ የተሰበሰበው ገንዘብ 10 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መድረሱን የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት አስታወቀ።

የፅህፈት ቤቱ ሰራተኞችና አመራሮች በ2009 በጀት ዓመት በተከናወኑ ስራዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በተለይም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ ቃል ከገባው ገንዘብ በ2009 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ ከ1 ቢሊየን 273 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ፅህፈት ቤቱ ያወጣው መግለጫ ያሳያል።

የተሰበሰበው ገንዘብም የእቅዱን 72 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑ ነው ለውይይት በቀረበው ሪፖርት ላይ የተጠቀሰው።

በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን 4 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማሰባሰብ ታቅዶ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ተመላክቷል።

በፌዴራል፣ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በተካሄደው የቦንድ ሽያጭ 103 ሚሊየን ብር፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የቶምቦላ ሎተሪ ሽያጭ 60 ሚሊየን ብር ተገኝቷል።

በታላቁ ሩጫ 4 ሚሊየን ብር ከህብረተሰቡ የተሰበሰበ ሲሆን፥ የንግዱ ማህበረሰብ በፅህፈት ቤቱ ለሚዘጋጁት የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች በቁሳቁስ ጭምር ድጋፍ እያደረገ መሆኑ በሪፖርቱ ቀርቧል።

ፅህፈት ቤቱ 8 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የነበረውን አጠቃላይ ተሰብሳቢ ገንዘብ በ2009 በጀት ዓመት ወደ 10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለማድረስ አቅዶ 10 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ማሰባሰቡ ነው የተነገረው።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ አሁንም የቦንድ ግዥ እያካሄደ መሆኑን የፅህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ ገልፀዋል።

ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከባለሃብቶች ቃል የተገባው ገንዘብ በተሟላ መልኩ ገቢ እንዲደረግ በጥብቅ የመከታተልና አዳዲስ ባለሃብቶችንና የመንግስት ሰራተኞች በቦንድ ግዥ እንዲሳተፉ ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዳያስፖራውን በቦንድ ግዥ በማሳተፍ የተገኘው ገቢ በ2009 በጀት ዓመት ከተያዘው እቅድ በላይ የተሰበሰበ ቢሆንም፥ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ግን ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ አማራጭ የገቢ ማግኛ መንገዶች በተጠናከረ ሁኔታ አለመተግበራቸውንና በአንዳንድ ክልሎች የህዳሴው ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ፅህፈት ቤቶች የተደራጁ አለመሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ በሪፖርታቸው ላይ ጠቅሰዋል።

የፅህፈት ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች የተሟላ ክትትልና ድጋፍ ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች እንደነበሩባቸው ያነሱት ወይዘሮ ሮማን፥ በ2010 በጀት ዓመት በተቋሙ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም በህዝብና በመንግስት የተጣለባቸውን አደራ ማሳካት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)