ዜና ዜና

ከአማራ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ከአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከቦንድ ሽያጭ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለፀ።

የክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ላቀ ጥላዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት አመቱ ከቦንድ ሽያጭ 94 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ቢታቀድም ከተጠበቀው በላይ አፈፃፀም ተመዝግቧል ።

በዚህም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 100 ሚሊዮን 743 ሺህ ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

"የህዳሴው ግድብ የድል ችቦ በክልሉ በሁሉም ዞኖች መዘዋወሩና የግደቡ መሰረት የተጣለበት 7ኛ ዓመት በህዝብ ንቅናቄ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩ በገቢ አሰባሰቡ የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ አስችሏል" ብለዋል ።

የመንግስት ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ ባለሃብቶችና ነዋሪዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት በቦንድ ግዥው መሳተፋቸውን ተናግረዋል ።

በበጀት አመቱ በገቢ አሰባሰቡ ሂደት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የተቋማት በቅንጅት አለመስራት ተጠቃሽ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው በተያዘው በጀት አመት ማስተካከያ በማድረግ የበለጠ አፈፃጸም ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለፃ የግድቡ ግንባታ የሀገሪቱን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት መንፈስ ይበልጥ ያስተሳሰረና የአለምን ትኩረት የሳበ ሆኖ ተስተውሏል ።

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አለምነው መኮነን ለህዳሴው ግድብ ማሰሪያ በሶስት ዙር ከ10 ሺህ ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈፀማቸውን ተናግረዋል ።

የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እስኪጀምር አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ቦንድ በመግዛት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል ።

"ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ የሚያሸጋግር ሀውልት በመሆኑ የጀመርኩትን ድጋፍ አጠናክሬ እቀጥላለሁ" ያለው ደግሞ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ደሳለኝ ካሴ ነው።

ለአምስት ዙር የወር ደሞዙን በማዋጣት እስካሁን የቦንድ ግዥ መፈጸሙን ወጣት ደሳለኝ ገልጿል።

ከክልሉ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ እንዳመላከተው የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከቦንድ ሽያጭ፣ ከልገሳና ከልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛዎች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተሰብስቧል ።

የክልሉ አርሶ አደሮችም በአመታቱ ውስጥ ግድቡን ከደለል ሙላት ለመታደግ ያከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ከ23 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለው ታውቅል ።

ባህርዳር ነሃሴ 28/2010 (ኢዜአ)