ዜና ዜና

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ100 ቀናት ቆይታ ከኢኮኖሚው አንጻር

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ100 ቀናት የስራ ጊዜ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅጣጫ ሊያስቀይሩ የሚችሉ ውሳኔዎች የተወሰኑበት መሆኑ ተነግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚሁ ቀናት በኢኮኖሚ ትብብሮች የተገኙ ድጋፎች የውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያውን አዳክሞታል።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የፈጠረችው ሰላምም የኢኮኖሚ ትንበያዋን መልካም አድርጎላታል።

በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት የትንበያም ሆነ የአቅጣጫ አዲስ ነገሮች የታዩበት ሆኗል የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ100 ቀናት የስራ ጊዜ።

ዲፕሎማሲው ሲሰምር፣ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ነዳጅ ሲገኝ፣ በኢትዮጵያ ባልተለመደ ሁኔታ የልማት ድርጅቶች ለግሉ ዘርፍ በአክስዮን እንዲተላለፉ ሲወሰን፣ ስለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ብዙ ተስፋዎች ታይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን በመጡ በ98ኛ ከኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አስመራ ላይ ተገናኝተው ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል አስመዝግበዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ተገናኝተው ማውራታቸው ሲሰማ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀን የኢትዮጵያ ዶላር ቦንድ በ10 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ጥሩ ዋጋ አገኘ የሚሉ ዜናዎችም ተበራክተዋል።

ይህ ለሀገሪቱ ለኢኮኖሚ ገጽታዋ ትልቅ ነገርን ያመጣ ነው ተብሎለታል።

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2014 በዓለማቀፍ የፋይናንስ ገበያ አንድ ቢሊዮን ዩሮን የሚያወጣ ቦንድን አቅርባ ነበር ገንዘቡም በ10ኛው ዓመት የሚመለስ ነው ተብሏል፡፡

ታዲያ ከዓለማቀፍ ገበያ ገንዘቡን የተበደሩ ሀገራት የውስጥ ፖሊቲካቸው መልካም ሲሆን አበዳሪዎች በሀገሪቱ መተማመን ያድርባቸዋል ሌላ ገንዘብን ለማቅረብም ይነሳሳሉ እንዲሁም ከብድር መመለሻው በፊት ገንዘቡን ከፈለጉት ቦንዱ የተሻለ ዋጋ ስለሚያወጣላቸው ለሌላ አካል ማቅረብ ይችላሉ።

ኢትዮጵያና ኤርትራ እሁድ ዕለት ሲታረቁም የሆነው ይሄው ነው፤ ከእርቁ የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ስለሚኖር የሸጠችው ቦንድ ጥሩ የገበያን ዋጋን አገኘ ኢንቨስተሮችም በብድር መላሽነቷ የተሻለ መተማመንን ማግኘታቸውን በናይሮቢ ያለው ስታንቢክ ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚስት ጂብራን ቁሬይሺ ተናግሯል።

ከወራት በፊት የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ይህም ያስከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነገሮችን የተገላቢጦሽ አድርጓቸው ነበር።

ከሀገራት ጋር ሰላም ሲወርድ የጦር መሳርያ ወጭ ሰለሚቀንስ የኢኮኖሚ ትንበያውን መልካም ያደርጋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ ያበሰሩት ነገርን ለኢኮኖሚው ተስፋ ሰጭነት የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው።

የሀገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪ የሚጠበቅበትን የውጭ ምንዛሬ ማምጣት ተስኖት አለመረጋጋቱም ተጨምሮበት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ከፍተኛ የሚባል ደረጃም ላይ መድረሱ የሚታወስ ነው።

ዘላቂ መፍትሄ አይሁን እንጂ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 2 ቢሊዮን ዶላርን በኢትዮጵያ ለሚደረግ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አንድ ቢሊዮን ዶላር ለውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል ኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እንደምታስቀምጥ ተናገረች።

ይህ ከሆነ ከሳምንታት በኃላ የአሜሪካን ግምጃ ቤት ተሰብስቦ የወለድ ምጣኔ ከፍ አለ ወይስ ዝቅ አለ በሚል የሚተራመሰውን ገበያ ዓይነት ኢትዮጵያ ውስጥም በጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ታይቷል በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከሰሞኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ መቀነሱም ተሰምቷል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አንድ የአሜሪካን ዶላር ቀድሞ ሲሸጥበት ከነበረው 36 ብር ወደ 29 ብር ከ50 ሳንቲም ድረስ ወርዶ ወደ ባንኮች ተመን እየተጠጋ መሆኑ ተሰምቷል።

ባለፉት መቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የስራ ቀናት በመንግስት እጅ ያሉት ሆቴሎች፣ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ እና የተለያዩ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች በግንባታና አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉትንም ያከትታል በከፊል ወይንም ሙሉ ለሙሉ በአክስዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክስዮን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች እንዲተላለፍ መወሰኑም ዋነኛው ጉዳይ ነበር።

መንግስት እንዲቆጥብም የውጭ ጉዞን ጨምሮ ብዙ ወጪዎች ገደብ እንዲጣልባቸው እንደተደረገ መገለጹም ይታወሳል።

 አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)