ዜና ዜና

በባሌ ዞን ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ነፃ የዓይን ህክምና አገልግሎት አገኙ

በባሌ ዞን ከአንድ ሺህ 300 ለሚበልጡ ሰዎች ነፃ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ተሰጠ ፡፡

የቀዶ ህክምና አገልግሎቱ በነፃ የተሰጠው "ቻሪቲ ዴቬሎፕመንት አሶስዬሽን" / ሲዲኤ/ የሚባል ግብረሰናይ ድርጅት የህክምና ቡድን ከባሌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ነው ፡፡

የሲዲኤ ድርጅት አስተባባሪ አቶ ካቦ አብዱረህማን ለኢዜአ እንደገለፁት ሰባት ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎችን ያከተተው የሕክምና ቡድን ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በባሌ ዞን ጊኒር፤ ደሎመናና ጎባ ሆስፒታሎች በዘመቻ መልክ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል ፡፡
እስከ አሁን በተደረገው እንቅስቃሴም በዞኑ በእቅድ ተጠቃሚ ለማድረግ ከተያዘው 2ሺህ 500 ውስጥ 1ሺህ 350 የሚሆኑ ሰዎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ፡፡

በቀጣይ ሳምንትም በባሌ ሮቤ ሆስፒታል ላይ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ አስተባባሪው ተናግረዋል ፡፡

ከቀዶ ህክምናው በተጓዳኝ የትራኮማ በሽታን ጨምሮ የአላርጂክ፣ የቅርበትና የርቀት እይታ ችግር የነበረባቸውን ከ600 በላይ ሰዎች የዓይን ሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡

የባሌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ቶሎሳ በበኩላቸው በተሰጠው የቀዶ ህክምና አገልግሎት ከሕመማቸው የሚፈወሱ ወገኖች ራሳቸውን ችለው በመንቀሳቀስ ምርታማ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ፡፡

ምክትል ኃላፊው እንዳሉት በቡድኑ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት በዞኑ በሚገኙ ሆስፒታሎች በቋሚነት የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች ተጨማሪ ልምድ እንዲቀስሙ እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት ሰዎች መካከል የጎባ ከተማ ምዕራብ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከበደ ታደሰ በሰጡት አስተያየት አይናቸው ለሶስት ዓመታት በሞራ በመጋረዱ የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው በሰው እርዳታ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል ፡፡

በአሁኑ ወቅት የሕክምና ቡድኑ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ባደረገላቸው የሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና እይታቸው ዳግም በመመለሱ መደሰታቸውን ተናግረዋል ፡፡

ሌላው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ ፋጡማ ከድር በሰጡት አስተያየት ከአቅም ማነስ የተነሳ ከዚህ በፊት የተሻለ ህክምና ወደሚሰጥበት የጤና ተቋም መሄድ ባለመቻላቸው ለሁለት ዓመት እንቅስቃሴያቸው በቤት ውስጥ ተገድቦ እንደነበር ተናግረዋል ፡፡

ወይዘሮዋ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በተደረገላቸው የዓይን ቀዶ ህክምና እይታቸው ተመልሶ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

ሲዲኤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ስድስት ዓመታት ባደረገው የአይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ከ14 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡
ህዳር 4/2010/ኢዜአ