ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም

ግብርናችንን በማዘመን የአገራችንን የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር እናፋጥን!

 

ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የአርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በዓል  ከዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዳማ ከተማ በደማቅ ስነሥርዓት በመከበር ላይ ይገኛል። የበዓሉ ዋና ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ አርሶ አደሮችንና ከፊል አርብቶ አደሮችን  በማበረታታት ወደ ባለሀብትነትና ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እንዲሸጋገሩ ማትጋት ነው፡፡

 

በመሆኑም በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ዘመናዊ የግብርና አሠራሮች የግብርና ምርታቸውንና ምርታማነታቸውን በማሳደግ የላቀ የግብርና ልማት ውጤት ያስመዘገቡ ሞዴል አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች እንዲሁም እነሱን በመደገፍ ለውጤት ያበቁዋቸው የልማት ሠራተኞች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም ባለሃብቶችና ልዩ ልዩ ተቋማት በበዓሉ ላይ ከኢፌዴሪ ጠ/ሚ አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ዕጅ ሽልማቶቻቸውን ይቀበላሉ። የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችንና ከባለሙያዎች የሚሰጣቸውን  የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በአግባቡ በመጠቀም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ወይም ጥሪት ያፈሩ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ወደ ባለሃብትነት የሚሸጋገሩበት ዕለት በመሆኑም በዓሉ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።

 

ከተሸላሚዎቹ  መካከል ሴቶች እና ወጣቶች የሚገኙበት መሆኑም ታላቅ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ ሀብታቸውን በግብርናው ልማት ዘርፍ በማዋል ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉና ዕሴት ወደሚጨምሩ የተለያዩ የግብርና ልማት ኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራዎች የተሸጋገሩ፣ ለወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ባለሃብቶችም የምንኮራባቸው የልማት አርበኞቻችን በመሆናቸው የዕለቱ ተሸላሚዎች ይሆናሉ።

 

እንደሚታወቀው በሀገራችን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥና በየደረጃው ያለውን ህዝብ ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተነደፈው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲያችንንና ስትራቴጂዎቻችንን ትክክለኛነትና ውጤታማነት በተግባር ከሚመሰክሩልን ዕውነታዎች መካከል አንዱ በየዓመቱ ምርትና ምርታማነታቸውን እያሳደጉ፣ ኑሯቸውን እያሻሻሉና ሃብት እያፈሩ ወደባለሃብትነት የሚሸጋገሩ እነኚህ የልማት ጀግኖቻችን ናቸው፡፡

 

በአጠቃላይ በአነስተኛ አርሶ አደሮቻችንና አርብቶ አደሮቻችን እጅ ሃብት እየተፈጠረ መሄዱ እና ወደ ባለሀብትነት በሂደትም ወደኢንዱስትሪ የሚያደርጉት ሽግግር የነገ መዳረሻችንን ከወዲሁ የሚያሳይ ነው፡፡።

የኢፌዴሪ መንግሥት ለመላው የአገራችን አርሶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች እንኳን ለበዓሉ አደረሳችሁ እያለ በስራ ትጋታቸው ተሸላሚ የሆኑትን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ይላል፡፡ በዚህ አጋጣሚም ከአርሶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች ጎን ሳይለዩ እየደገፏችሁ ያሉት የልማት ጣቢያ ሰራተኞች፤ የግብርና ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች፣ እንዲሁም በተለያየ መልክ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ያሉ ባለሃብቶችና ልዩ ልዩ ህዝባዊና መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም መላው ህዝባችን ወደኢንዱስትሪ ልማት የምናደርገውን ሽግግር ለማሳካት ጥረታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪውን ያቀርባል!