ዜና ዜና

በክልሉ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ፡፡

በደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽነር ሀባስ መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ካፒታላቸውን በማስመዝገብ ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶች ቁጥር ከ173 በላይ ነው።

ባለሃብቶቹ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ12 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ገልጸው፣

በጠቅላላው 1 ቢሊዮን 865 ሚሊዮን ብር በማስመዝገብ ፈቃድ የወሰዱት ባለሀብቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ የሚሰማሩ ናቸው።

በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ውስጥ በኢንቨስትመንት መስክ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች በተያዘው ዓመት 10 ሺህ 557 ሄክታር መሬት በከተማና በገጠር ለመስጠት ቦታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

እንደኮሚሽነር  ገለጻ፣ ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት ለመሰመራት በገቡት ውል መሰረት ወደ ሥራ ያልገቡና ልማት ያልጀመሩ 52 ፕሮጀክቶች በጥናት ተለይተው ለ18ቱ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። 

ከእዚህ በተጨማሪ አንድ ባለሀብት ከወሰደው መሬት እንዲቀነሰበት የተደረገ ሲሆን በኢንቨስትመንት ሥራ ያልተሰማሩ 33 ባለሀብቶችም ውላቸው እንዲቋረጥ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ 

በደቡብ ኦሞ ዞን በግብርና መስክ ለመሰማራት የተወሰዶ በባለሀበት ተወስዶ  ወደ ስራ ያልገባ 50 ሺህ ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉንም ተናግረዋል

ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የመንገድ ችግር ለመፍታት በቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትና በክልሉ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን በኩል የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

የሲዳማ ዞን ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ወልደሚካኤል በበኩላቸው "ባለሀብቶች ወደ ዞኑ መጥተው በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሰማሩ ለማድረግ የማስተዋወቅ ሥራ መሰራቱን" ገልጸዋል፡፡

በይርጋለም  የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር ተያይዞ በአካባቢው መዋለንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና እስካሁንም 20 ባለሀብቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ለእዚህም በዞኑ በኩል የመሬት ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው አቶ ብርሀኑ የገለጹት።

ሀዋሳ ጥር 8/2010(ኢዜአ)