ዜና ዜና

በደቡብ ክልል ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በደቡብ ክልል በተዘዋወረባቸው ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከ1 ቢሊየን 287 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን በክልሉ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው እንደገለፁት፥ ዋንጫው እስካሁን በክልሉ 13 ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች ተዘዋውሯል።

''ህዳር 29 2009 ዓ.ም ከሐረሪ ክልል የተረከብነው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ በሚኖረው ቆይታ 500 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ ነበር'' ብለዋል፡፡

ዋንጫው እስካሁን በተዘዋወረባቸው ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከፍተኛ የህዝብ መነሳሳት በመፈጠሩ ከእቅዱ ከእጥፍ በላይ ብልጫ ያለው ድጋፍ በስጦታና በቦንድ ግዢ ማሰባሰብ ተችሏልም ብለዋል፡፡

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ የህዝብ አቀባበል የተደረገለት ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ የልማት መነቃቃትን በመፍጠርና የይቻላል መንፈስን በማጎልበት ረገድ ጉልህ ሚና መጫወቱን ገልፀዋል።

በተጨማሪም የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል በማጎልበት ኢኮኖሚያዊ አቅሙን እንዲያጠናክር አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በደቡብ ክልል የሚያደርገውን ቆይታ ለማጠናቀቅ አሁን ያለበት ሲዳማ ዞንና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እንደሚቀሩት ከዳይሬክተሩ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

 አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2010 (ኢዜአ)