ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ሀምሌ 07 ቀን 2009 ዓ.ም

በተባበረ ክንድ የክረምት ሥራችን የግብርና ምርታማነታችንን እናጎልብት!
ግብርናችን፣ በተለይም በአነስተኛ የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የምናካሂደው የግብርና ሥራችን የአገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑ ይታወቃል። የአገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚቻለው በቅድሚያ በአነስተኛ የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በሚካሄድ የግብርና ልማት መሆኑ ታምኖበት ላለፉት 26 ዓመታት በተለይም ላለፉት 15 ዓመታት በተሰራው መጠነ ሰፊ ሥራ ዘርፉ በአማካይ የዘጠኝ በመቶ እድገት ማስመዝገብ ችሏል። በዚህም ለአገሪቷ አጠቃላይ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት መሰረት መጣሉ ይታወቃል።

በአጠቃላይ አገራችን በአንድ በኩል ፈጣን ዕድገት፣ በሌላ በኩል ፍትሃዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ እና በየዓመቱ ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የቻለችው በዋነኛነት በአነስተኛ ማሳ ላይ በተሰማሩ አርሶ አደሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ በተሰራው ሥራ ነው።

መንግሥት የነደፈውን ፖሊሲና ስትራቴጅዎች ሥራ ላይ በማዋል የራሳቸውንና የቤተሰቦቻውን ህይወት ከመለወጥ ባለፈ ለአገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱት መላ የአገራችን አርሶ አደሮች ፣ እንዲሁም ዘወትር ከእነርሱ ጎን ሳይለዩ ምክር እና ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ለውጤት ላበቋቸው የኤክስቴንሽን ሠራተኞች፣ የግብርና አመራርና ባለሙያዎች በሙሉ በዚህ አጋጣሚ መንግሥት የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል።

ሆኖም በአገራችን መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ከማረጋገጥ አኳያ አሁንም የሚቀሩን በርካታ ሥራዎች አሉ። በመሆኑም የዘንድሮውን የክረምት ወራት እንደ አንድ ተጨማሪ ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል። የሚባክን ውሃ ሳይኖረን፣ የሚባክን ጉልበት ሳይኖረን ምርትና ምርታማነታችንን ማሳደግ ለሚያስችሉን ለውሃ እቀባና ለአፈር ጥበቃ ለመሳሰሉ ሥራዎች ልናውለው ይገባል።

ከዚህ አንጻር በአንዳንድ አካባቢዎች እንደተስተዋለው የከተማ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና የመከላከያ ሠራዊታችን አባላት እንዲሁም በርካታ ወጣቶች በችግኝ ተከላ፣ በጎርፍ አደጋ እና በተምቺ ወረርሽኝ መከላከል እና በመሳሰሉት ሥራዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። የኢፌዴሪ መንግሥት ለነዚህ አገር ወዳድ ወገኖች ላቅ ያለ ምስጋናውን እያቀረበ፣ መላው ህዝባችን ይህን መሰሉን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ለህዳሴያችን መሰረት ለሆነው ፈጣን እና ፍትሃዊ እድገት መረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪውን ያስተላልፋል።