ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ሚያዚያ 05 ቀን 2010 ዓ.ም

አንድነታችንን በማጠናከር ልማታችንን እናፋጥን!

አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች። በአገራችን አስተማማኝ ሰላም፤ ዘላቂ ልማት፣ መሰረተ ሰፊ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደርን ከመቼውም በላቀ አፈጻጸም ተግባራዊ ለማድረግ በመንግሥት የተጀመረው አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በላቀ የህዝብ ተሳትፎ ለድል እንደሚበቃም መንግሥት በጽኑ ያምናል፡፡

ሰላም በሌለበት ስለልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ ይቅርና በህይወት መኖርም አጠያያቂ ነው። በመሆኑም በአገራችን ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ሳቢያ ተፈጥሮ የነበረውን መቃቃርና ጥርጣሬ ከመሰረቱ ለማስወገድና ሰላማችንን ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ ይቻል ዘንድ በህዝቦች መካከል አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል በአገራችን አስተማማኝ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው ህዝቡ የሚያነሳቸው ተገቢ ጥያቄዎች ምላሽ ሲያገኙ እና ፍትህ ሲሰፈን መሆኑን በመገንዘብ መንግሥት ከመላው ህዝቦቻችን ጋር በመሆን አስፈላጊውን ሥራ በማከናወን ላይ ነው፡፡

ልማታችን፣ መላውን ህዝብ ለልማቱ ባበረከተው አስተዋጽኦ ልክ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ የተያያዝነውን አገራዊ ግብ በሚያሳካ መልኩ የሚፈጸም፣ እና በፍትሀዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ መንግሥት ይገነዘባል።

ዴሞክራሲያችን፤ በብዝሀነት ላይ የተመሰረተ፣ ህዝብን ያሳተፈና ባለቤት ያደረገ መሰረተ ሰፊና አሳታፊ እንዲሆን፣ በአመለካከቱ የተስተካከለና በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ የሚሰጥ ህብረተሰብ የመገንባት ስራ፣ ዲሞክራሲን ባህል ከማድረግና ተቋማትን ከማጠናከር ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ ለአስተማማኝ ሰላም መሰረት የሆነና ሁሉንም በየደረጃው በፍትሀዊነት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ልማት ማረጋገጥ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን፣ የህግ የበላይነትን፤ የግልጸኝነትና የተጠያቂነት ስርአትን ለማስፈን፣ እና የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ በሚፈለገው ደረጃ ለማረጋገጥ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ለማረጋገጥ ይወዳል።

ችግሮቻችን ሁሉ የሚፈቱት ግን በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ህዝብ ባሳተፈ ርብርብ መሆኑን በውል መረዳት ይገባል፡፡

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ እና ህዝባዊ ማህበራት፣ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል እና ዜጎች፣ በአጠቃላይ ምልአተ ህዝቡ መንግሥታችን እያካሄደው ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ እንዲረባረቡ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያውያን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወሰነው በማንም ሳይሆን ዛሬ የገዛ ልጆቿ በሚያደርጉት አስተዋጽኦ ልክ ብቻ ነው። ዛሬ እያካሄድነው ያለው የለውጥ እንቅስቃሴም መነሻውም ይሁን መድረሻው የኢትዮጵያን ህዝቦች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡

በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን፦ በመላው ዓለም ዘንድ ልዩ የሚያደርጉንን የመቻቻል፣ የመተሳሰብ እና የመተባበር እጹብ፣ ድንቅ እሴቶቻችንን ጠብቀን፣ በአንድነት እና በመፈቃቀር እጅ ለእጅ ተያይዘን ልማታችንን እንድናፋጥን መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡