ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ግንቦት 04 ቀን 2009 ዓ.ም

በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎቻችን የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ከማብቃቱ በፊት ወደአገራቸው እንዲመለሱ ሁላችንም እንረባረብ!
የሳዑዲ መንግስት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የሁሉም አገራት ዜጎች ካለፈው መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በ90 ቀናት እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል። ጉዳዩ እንደታወቀ የኢፌዴሪ መንግሥት ሳይውል ሳያድር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ልዩ ልዩ ተግባራትን በማካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ለተመላሾች በሚወጡበት አገር ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ ወደአገር እስኪመለሱና ብሎም ወደየቀያቸው ሲመለሱ አቅም በፈቀደው መልኩ በዘለቄታ እስከሚቋቋሙበት ድረስ ከክልል መንግሥታት ጋር በመሆን ዝርዝር ጉዳዮችን በማጥናትና ሥርዓት በማበጀት ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል፡፡

በሳውዲ ዓረቢያም አንድ ግብረ ሃይል በማቋቋም በዚያ የሚገኙ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎቻችን የመውጫ ቪዛ የሚያገኙባቸው ተንቀሳቃሽ ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን የጉዞ ሰነድ እና መረጃ እየሰጠም ይገኛል። ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የተለያዩ የመገልገያ ዕቃዎችን ያለቀረጥ እንዲያስገቡም መንግሥት ፈቅዷል፡፡

የመንግስት ፍላጎት ከሳዑዲ ተመላሽ ዜጎቻችን አንዳችም ዓይነት ጉዳት እና እንግልት ሳይደርስባቸው በተሰጣቸው የእፎይታ ጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም በእስካሁኑ ሂደት የተወሰኑ ዜጎቻችን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፤ አሁንም በየዕለቱ በመመለስ ላይ ናቸው። ይሁን እንጅ የተመላሾቹ ቁጥር ከሚጠበቀው አንጻር ሲታይ አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ምክንያቱም ዜጎቻችን የሳዑዲ መንግስት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ወደ አገራቸው ካልተመለሱ አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ የዜጎቻችን ሰብዓዊ መብቶቻቸው ይጣሳሉ፣ ንብረቶቻቸው ይወረሳሉ፣ ለእንግልት ይዳረጋሉ። በመሆኑም በሳዑዲ የሚገኙት ዜጎቻችን ይህንኑ ከወዲሁ ተገንዝበው በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በቀሪዎቹ ቀናት ፈጥነው ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡

የጊዜ ገደቡ ሳይጠናቀቅ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ በማድረግ በኩል በተለይ ወላጆች ለልጆቻቸው ደህንነት ሲሉ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ የሚገባቸው ሲሆን መንግሥት፣ ሚዲያዎች፣ ማህበራት፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና መላው ህዝባችን የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ዜጎቻችንን ቶሎ እንዲመለሱ በማድረግ በኩል የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።

ህገ ወጥ ስደት ዘመናዊ ባርነት በመሆኑ ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እና ደላሎችን ለመቆጣጠር የሚካሄደውን ጥረት መላው ህዝባችን አጠናክሮ እንዲቀጥል በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል። ስደት ለአገርና ለወገን ውርደት ነው! በአገር ሰርቶ መለወጥ ግን ኩራት ነው!