ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ህዳር 01 ቀን 2010 ዓ.ም.

ድሎቻችንን መጠበቅ የሁላችንም ድርሻ ነው!

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው፣ የአገራቸውን ጉዳይ ደግሞ በጋራ የሚወስኑበትን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስርተው መተዳደር ከጀመሩ አስርተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የቅራኔ ምንጮች የነበሩ ጉዳዮችን ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋታቸውም አገራችን ኢትዮጵያ ሰላም በራቀው የአፍሪካ ቀንድ እየኖረች በአንጻራዊነት ከመቼውም ጊዜ የተሻለች ሰላማዊት አገር መሆን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገራትም የሰላም ዘብ መሆን ችላለች።

ህዝቦቻችን ሰላም በማግኘታቸውም ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ልማት በማዞር ልማታቸውን እያፋጠኑና ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ። የልማቱ ድምር ውጤትም አገራችንን በማያቋርጥ ፈጣን የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገኝ አስችሏታል። ይህም ለዘመናት ትታወቅበት የነበረውን መጥፎ ገጽታ ቀይሮት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ የዓለም አገራት በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ አገር አድርጓታል። ከድህነትና ኋላቀርነት የምትላቀቅበትና ወደከፍታ ማማ የምትወጣበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑንም በተግባር ማረጋገጥ ችላለች፡፡

እነዚህና ሌሎችም በርካታ ድሎች የመመዝገባቸውን ያህል ግን በየጊዜው የተከሰቱ ፈተናዎችም አጋጥመዋል። ዋናው ነገር ያጋጠሙንን ችግሮች ሁሉ በመንግሥትና በህዝቦቻችን የጋራ ትግል እየፈታናቸው መምጣታችን ነው።

አሁን ባለንበት ወቅትም ቢሆን የሰላማችንን፣ የፈጣን ዕድገታችንን እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችንን ሂደት እየተፈታተኑ ያሉ እንቅፋቶችን ፊት ለፊት እየተጋፈጥን ነው የምንገኘው፡፡ ህዝባችንን እያማረሩ ያሉ የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ሌሎችም በጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ የተለዩ ልዩልዩ ችግሮች በሚፈቱበት አግባብ ላይ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደሥራ ለመግባት ተሞክሯል። ከተከናወኑት አበረታች ሥራዎች መካከልም በወጣቶች ላይ በስፋት የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተደረጉ ጥረቶችን በአብነት ማንሳት ይቻላል። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትም እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ሲሆን የህብረተሰቡን እርካታ ማረጋገጥ ይቀረናል በሚል ተጨማሪ ሥራዎችን በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሥርዓቱ ጤናማ ሆኖ መቀጠል የግል ጥቅማቸውን እንደሚያቋርጠው የተረዱ ያለአግባብ የመበልጸግ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ከጸረ ሰላም ሀይሎች ጋር በመቀናጀት የተጀመረውን ትግል ለማፈን ሲፍጨረጨሩ ታይተዋል። በሰላማዊ ህዝቦች መካከል ቅራኔን እስከመፍጠርና የአገራችንን ሰላም እስከማደፍረስ ብሎም ገጽታዋን እስከማበላሸት የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ሞክረዋል።

ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባሮቹ ላይ የተጀመረው አገራዊ ትግል የአገራችን እና የህዝቦቿ ህልውና ጉዳይ መሆኑን ነው። እንደዚያው ሁሉ ብሄር ተኮር ግጭቶች እንዲከሰቱና አለመረጋጋት እንዲኖር ምክንያት የሆኑትን ሃይሎች ለማስወገድ የተጀመረውን ትግል ከዳር ማድረስ ለመንግሥት አካላት ብቻ የሚተው ተልዕኮ አለመሆኑንም በውል መገንዘብ ያሻል።

የአገራችን ሰላም በአስተማማኝ መልኩ እንዲጠበቅ፣ የተጀመረው ተስፋ ሰጪ እድገታችን እንዲፋጠን ብሎም ፈጣኑን የእድገት ጉዟችንን ለመቀልበስ እየተፍጨረጨረ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢ እና የጸረ ሰላም ሃይል በአስተማማኝ ሁኔታ ድባቅ መምታት የሚቻለው እንደወትሮው ሁሉ በመንግሥትና በመላው ህዝባችን በሚካሄድ የተቀናጀና የጋራ ርብርብ ብቻ ነው።

በመሆኑም መላው የአገራችን ህዝቦች፣ በመንግሥት የተጀመረውን የጸረ- ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደወትሮው ሁሉ በመቀላቀልና በባለቤትነት በመምራት ከዳር እንዲያደርሱትና ለድል እንዲያበቁት መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል። ያስመዘገብናቸውን ድሎች መጠበቅና ማስቀጠል የምንችለው እንደወትሮው ሁሉ በህዝቦቻችን የላቀ ተሳትፎና ባለቤትነት ብቻ ነውና!