ዜና ዜና

ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር ብቻ ከቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም የወጪ ንግድ 67 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።

ኢትዮጵያ ባለፈው ኃምሌ ወር ብቻ ለውጭ ገበያ ካቀረበችው ቡና፣ ሻይና፣ ቅመማቅመም 67 ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር ገቢ ማግኘቷን የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ።

ከዚህ ውስጥ 65 ነጥብ 69 ሚሊዮን ዶላሩ የተገኘው ከቡና የወጪ ንግድ ነው።

ባለፈው ኃምሌ ወር 2010 ዓ.ም ብቻ 18 ሺህ  ቶን ጥሬ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የተገኘ ሲሆን ገቢው ለማግኘት ከታቀደው አንጻር ግን ያነሰ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳለው በወሩ ተይዞ የነበረው እቅድ ከ22 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 81 ነጥብ 58 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ነበር።

በሌላ በኩል ባለፈው ኃምሌ ወር 1 ሺህ 210 ቶን ቅመማ ቅመም ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 61 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገባት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም 816 ነጥብ 07 ቶን  በመላክ 850 ሺህ ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

ከሻይ ቅጠል ምርት የወጪ ንግድ አንፃርም በኃምሌ ወር 108 ነጥብ 37 ቶን በመላክ 260 ሺህ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 188 ነጥብ 15 ቶን በመላክ 330 ሺህ ዶላር ገቢ ማድረግ ተችሏል፡፡

ሀገሪቱ በአጠቃላይ ባለፈው ኃምሌ ወር 24 ሺህ ቶን የሚጠጋ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም በመላክ 83 ነጥብ 45 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳ  19 ሺህ ቶን ያህል በመላክ 66 ነጥብ 87 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች።

ክንውኑ ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር በመጠን 79 ነጥብ 3 በመቶ፤  በገቢ ደግሞ 80 ነጥብ 14 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ሀገሪቱ በአጠቃላይ ከቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም የወጪ ንግድ ያገኘቸው 854 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ መዘገባችን ይታወሳል።

ከዚህ ውስጥ 838 ሚሊዮን ዶላሩ የተገኘው ከቡና መሆኑን የባለሰልጣኑ የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳሳ ዳንጊሶ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልፀዋል።

 አዲስ አበባ  ነሀሴ 4/2010(ኢዜአ)