ዜና ዜና

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ 71 የመርከብ ባለሙያዎችን አስመረቀ።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ ለ16ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 71 የመርከብ ኤሌክትሪካል ቴክኒሻን ባለሙያዎች ዛሬ አስመረቀ።

ተመራቂዎቹ በኤሌክትሪካልና በኤሌክትሮ መካኒካል ኢንጅነሪንግ የሙያ መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ቀደም ሲል ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የያዙ መሆናቸው ታውቋል።

የእለቱ ተመራቂዎች አካዳሚው ከተለያዩ የዓለም አገራት የመርከብ ካምፓኒዎች ጋር ባለው ሰምምነት መሰረት በመንገደኞች፣ በእቃ ማጓጓዣዎች ( ካርጎ) እና በጦር መርከቦች ላይ የሚቀጠሩ ናቸው።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሃይል አሰልጥኖ በማቅረብ የአገሪቱን እድገት እየደገፈ ይገኛል።

በዓለም ደረጃ ያለውን የገበያ ፍላጎትና በመርከብ ኢንዱስትሪው ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከእስራኤል መንግስት ጋር በመተባበር ሙያተኞችን እያፈራ ይገኛል።

"አካዳሚያው የሚያስመርቃቸውን ሙያተኞች በአውሮፓ፣ አሜሪካና ሌሎች አህጉራት በሚገኙ የመርከብ ኩባንያዎች ባለፉት ዓመታት እያስቀጠረ ይገኛል" ብለዋል።

"ስልጠና የወሰዳችሁ የዛሬ ተመራቂዎችም ሙያው የሚጠይቀውን ስነ-ምግባር በመላበስ በምትሰማረቡት ሁሉ የአገራችን አምባሳደርነታችሁን ማስመስከር አለባችሁ " በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የመርከብ ቴክኒሻን ለመሆን የሚያበቃቸውን በተግባር የተደገፈ እውቀትና ክህሎት የጨበጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተመራቂዎች ዩኒቨርሲቲውንና አገራቸውን ወክለው ስለሚንቀሳቀሱ ሙያዊ ብቃትን በማሳየት ለአገራቸው የገጽታ ግንባታ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በኤሌክትሮ ሜካኒካል ምህድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን ቀደም ሲል መያዙን የገለጸው  ተመራቂ ትንቢት ዳኛቸው እንዳለው በምሰማራባቸው አገራት ሁሉ የአገሬን ስምና ዝና ከፍ ለማድረግ እጥራለሁ ብሏል።

ኢትዮጵያን ወክሎ በመርከብ ኤሌክትሪካል ምህንድስና በተለያዩ የውጭ አገራት ለስራ መሰማራት መቻሉ እንደሚያኮራው የተናገረው ደግሞ ተመራቂ ሮቤል ይፍጠር ነው።

ለስራ በሚሰማራባቸው አገራት የሚያገኘውን ልምድና ተሞክሮ በመቅሰም ብቁ ሙያተኛ ሆኖ በመውጣት በዘርፉ ያለውን ውድድር ለማሸነፍ እንደሚሰራ ገልጿል።

አካዳሚው እስካሁን ከአንድ ሺህ 100 በላይ ባለሙያዎችን በማስመረቅ በአውሮፓ፣ አሜሪካና ሌሎች አህጉራት በሚገኙ የመርከብ ካምፓኒዎች በማስቀጠር ላይ ይገኛል።

 ባህር ዳር ነሃሴ 2/2010(ኢዜአ)