ዜና ዜና

የኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገለጸ

የኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ16 ቢሊዮን በላይ ብር መሰብሰቡን ገለጸ።

ክልሉ ለዘጠኝ መቶ ሺህ ገደማ ስራ አጥ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተገልጿል።

የክልሉ 8ኛ መደበኛ ጨፌ ጉባኤ በአዳማ ገልማ አባ ገዳ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የክልሉን የ2010 ዓ.ም በጀት አመት ሪፖርት ለጨፌው ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል።

በዚሁ መሰረት ገቢን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት 16 ነጥብ 186 ቢሊዮን ብር ከተለያዩ ምንጮች ገቢ ተሰብስቧል።

ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ከሰራባቸው ስራዎች መካከል የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ሲሆን፤ በዚህም ለ600 ሺህ ቋሚና ለ300 ሺህ ወጣቶች ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር እንደቻለ ገልጸዋል።

ይህም ሊሆን የቻለው በኢንቨስትመንት ስም በህገ ወጥ መልኩ ተይዞ የነበረ መሬት ለወጣቶቹ በማስተላለፍ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በህገ ወጥ መልኩ ተይዘው የነበሩ የማዕድን ስፍራዎች ለወጣቶች በማስተላለፍና በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ በማሰማራት የተገኘ ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት፤ በበጀት አመቱ በክልሉ ሰላምና ደህንነትን የማስከበርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል።

በዚህም ከአማራ፤ ከቤኒሻንጉል ጉምዝና ከደቡብ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚፈጠሩትን ግጭቶች ለመፍታት የተሞከረ ሲሆን፤ ከሱማሌ ክልል ጋር ያለውን ግጭት እልባት ለመስጠት ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

የግብርና ስራዎች የመንገድና የመጠጥ ውሃ፤ የትምህርትና የጤና ዘርፎችም በበጀት አመቱ በትኩረት የተሰራባቸው ዘርፎች መሆናቸቸውንም ለጨፌው አባላት አብራርተዋል።

በበጀት አመቱ 23 ነጥብ አራት ሚሊዮን ህዝብ በገጠርና በከተማ የንጹህ ውሃ መጠጥ ተጠቃሚ መሆን የቻለ ሲሆን፤ 213 አዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል።

ከዚህ ባለፈም ከዚህ በፊት መጠናቀቅ ያለባቸው13 ሆስፒታሎች ግንባታ የተጠናቀቁ ሲሆን 167 አምቡላንሶች በክልሉ ለሚገኙ የጤና ተቋማት ተሰራጭቷል።

ፕሬዝዳንቱም በአመቱ የፍትህ ዘርፉን ለማሻሻል ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ ከ16 ሺህ በላይ ታራሚዎች በይቅርታና በልዩ ሁኔታ ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ተናግረዋል።

የተሰሩ ስራዎች በአብዛኛው የተሻሉ ቢሆኑም አሁንም ከክልሉ የልማት ፍላጎቶች አንፃር ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ አንስተዋል።

ጨፌው ከሰዓት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቱን የሚቀጥል ሲሆን በክልሉ የ2011 በጀት ዓመት እቅድና በጀት ዙሪያ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

ሐምሌ 2/2010/ኢዜአ/