ዜና ዜና

ኤጀንሲው ከሰራተኞች የጡረታ መዋጮ ቆርጠው ያላስገቡ የግል ድርጅቶች 50 ሚሊየን ብር እንዲከፍሉ አደረገ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ካለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ ከሰራተኞቻቸው የጡረታ መዋጮ ቆርጠው ያላስገቡ ድርጅቶችን ኦዲት በማስደረግ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ማስከፈሉን የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

ለዚህም "ከአንድ ዓመት በፊት ለመከታተል የዘረጋሁት ቴክኖሎጂ ረድቶኛል" ብሏል ኤጀንሲው።

የኤጀንሲው የህግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሲሳይ፥ በድርጅቶቹ ላይ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ይናገራሉ።

በዚህ መልኩ የሰራተኞቻቸወን የጡረታ ክፍያ ከሃምሌ ወር ጀምሮ በተገቢው መንገድ ገቢ ያላደረጉ 60 የግል ድርጅቶች መኖራቸው ተርጋግጧል ብለዋል።

ድርጅቶቹ ላይ የኦዲት ስራ ከተሰራ በኋላም በባንክ ሂሳባቸው ላይ ከሚገኝ ገንዘብ 50 ሚሊየን 356 ሺህ ብር የሰራተኞች መዋጮ ገንዘብ እንዲቆረጥ በማድረግ ገቢ መደረጉንም አንስተዋል።

ኤጀንሲው በ2009 ዓ.ም የሰራተኞቻቸወን የጡረታ ክፍያ በተገቢው መንገድ ካላስገቡ 4 ሺህ 18 ድርጅቶችን ኦዲት በማድረግ ከ145 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማድረጉንም አስታውሰዋል።

ለዚህም ምክንያቱ በአዲሱ ቴክኖሎጂ ስርአት መሰረት ድርጅቶችን መከታተል በመቻሉ ነው ያሉት አቶ ግርማ፥ መከታተያው ድርጅቶቹን ወደ ስርአቱ ከማሰገባት አንጻር ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።

የቴክኖሎጂው ስርአት በዚህ መልኩ በመከታተል ለውጥ አምጥቷል ይባል እንጂ፤ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ገቢያቸውን የሚከታተሉ ሰራተኞች ግን የሉም የሚባል ደረጃ ላይ ነው።

እንደ አቶ ግርማ ገለጻ፥ በተዘረጋው ስርአት በመጠቀም ሰራተኞች በየወቅቱ የገባላቸውን የጡረታ መዋጮ መጠን ማወቅ ሲገባቸው ይህን ግን እየተገበሩ አደለም ይላሉ።

በግል ድርጅት የሚሰሩ ሰራተኞች በመዋጮው መለያ ቁጥራቸው ገቢያቸውን በማረጋገጥ መብታቸውን እንዲያስከብሩ ኤጀንሲው ጥሪ አቅርቧል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የግል ድርግቶች ሰራተኞች የጡረታ መዋጮ እየከፈሉ መሆኑን ከግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)