ዜና ዜና

በክልሎቹ ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ የተጎዳ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ተደርጓል

ብሔራዊ የብዝሀ ሕይወት ማካተቻና ማትጊያ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየሆነባቸው ባሉ አካባቢዎች ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ የተጎዳ መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነጻ መደረጉን የአካባቢ ደን ልማት እና የአየር ንብረት ለወጥ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የፕሮከክቱ ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ አብደታ ደበላ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ዓመታት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የብዝሀ ህይወት መመናመን በሚታይባቸው በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሶማሌ ክልሎች በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ነው ።

በፕሮጀክቱ የአካባቢ መራቆትና የአፈር መከላትን ለመከላከል በሚሰራው ሥራ በ34 ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ከ7 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ወጣቶቹና ሴቶቹ የተሰማሩባቸው የስራ መስኮች ንብ ማነብ፣ የእንስሳት መኖ ልማት፣ የአፈሪና ውሃ እቀባ፣ ደን ልማትና ጥበቃ እንዲሁም እንስሳት ማድለብ ናቸው።

"በቀጣይ በዘርፉ የሚሳተፉ ወጣቶችና ሴቶችን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ ከብዝሀ ህይውት ጥበቃ ኢንስቲትዩት፣ ከክልል ግብርና ቢሮዎችና ከምግብ ዋስትናና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጄንሲ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

አቶ አብደታ እንዳሉት፣ በብዝሀ ሕይወት ሀብት መመናመን የሚመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ብሔራዊ የብዝሀ ሕይወት ማካተቻና ማትጊያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ 19 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቧል ።

ከዚሁ ጎን ለጎን የተቀናጀ የስነ ምህዳርና የመሬት አስተዳደር አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በሚኒስቴሩ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ኃይሌ ናቸው።

"የተቀናጀ ዘላቂ የመሬት ልማትና አስተዳደር ለምግብ ዋስትና ማረጋገጥ" የሚለው ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረጋ ያለው ስነ ምህዳራቸው የተጎዳና የምግብ ዋስትናቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሱ ወረዳዎች ተመርጠው ነው።

ፕሮጀክቱ ከተያዘው 2010 ጀምሮ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሶማሌ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች በሚገኙ 12 ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

"በፕሮጀክቱ ከ140 ሺህ በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ሴቶችና ወጣቶች በቀጥታ ተሳታፊና ተጠቃሚ ይሆናሉ" ብለዋል ።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ 10 ሚሊዮን ዩሮ ተመድቧል።

በአንደኛ ዙር ተግባራዊ በሆነው በዚሁ ፕሮጀክት በአካባቢ፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና አያያዝ ላይ ለውጥ መምጣቱ ተመልከቷል ።

የካቲት 20/2010/ኢዜአ/