ዜና ዜና

በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ27 ሺህ ባላይ እናቶች በጤና ተቋም ወለዱ

በምዕራብ ወለጋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ከ27 ሺህ  ባላይ እናቶች በጤና ተቋም መውለዳቸውን የምዕራብ ወለጋ ዞን ጤና አጠባበቅ ፅህፈት ቤት አስታወቀ ።

 የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ከድር ሙዘይን  እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ስድስት ወራት ከ32 ሺህ በላይ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ ታቅዶ 27 ሺህ 600 እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።

 ክንውኑ ከዕቅዱ ጋር ሲታይ 73 በመቶ፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ10 በመቶ ያነሰ መሆኑን አቶ ከድር አመልክተዋል።

 "አምቡላንሶች ጊዜ ጠብቆ ብቃታቸው እንዲፈተሽ አለመደረጉና ሲበላሹ ወዲያው ጥገና አለማድረግ እናቶችን በወሊድ ወቅት ወደ ጤና ተቋም የማጓጓዝ አገልግሎቱን በሚፈለገው መጠን እንዳይሆን አድርጓል" ብለዋል ።

 ችግሩ በበጀት እጥረት የተፈጠረ መሆኑን ያብራሩት ኃላፊው ለመፍትሄው ከሚመከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

 በጤና ተቋም ማቆያ ቦታ ለወላድ እናቶች ይደረግ የነበረው እንክብካቤ በአብዛኛው ጤና ጣቢያ ላይ መቋረጡ ሌላው በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ማነስ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

 ለእዚህም ጽህፈት ቤቱ ሕብረተሰቡን በማስተባበርና የነበረው አሰራር በመመለስ በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ለመጨመር አቅዶ እየሰራመሆኑን ጠቁመዋል።

 አቶ ከድር እንዳሉት፣ በሀገሪቱ በተያዘው ስትራቴጂክ ዕቅዱ ከ100 ሺህ ነፍሰጡር እናቶች መካከል በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ከ421 በታች ለማድረስ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው።

 "ለእዚህም እናቶች  ማርገዛቸውን ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ የቅድመ ወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙና በጤና ተቋም እንዲወልዱ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል ።

 በዞኑ የቂልጡ ካራ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በዳሳ በሊና በወረዳው ባለፉት ስድስት ወራት 1 ሺህ 222 እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ መታቀዱንና 94 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

 በቂልጡ ካራ ጤና ጣቢያ የመጀመሪያ ልጃቸውን በሰላም የተገላገሉት ወይዘሮ አረጋሽ ተሾመ በበኩላቸው የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረጋቸውና የጤና ባለሙያን ምክርን ተግባራዊ በማድረጋቸው ጤናማ ልጅ ለመውለድ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

 ከዓመታት በፊት በአካባቢያቸው አገልግሎቱን በማጣት የተጎዱ እናቶችና ሕፃናት እንደነበሩ የገለጹት ደግሞ ሌላዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ ዘውዴ ሂርጳ ናቸው።

 በዞኑ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ወረዳ ያሉ ጤና ጣቢያዎች፣ በአራት የመንግስትና ሁለት የግል ሆስፒታሎች የማዋለድ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የዞኑ ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት መረጃ  ያመላክታል፡፡

ጥር 3/2010፤ኢዜአ