ዜና ዜና

በትግራይ ክልል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ቃል ከተገባው ገንዘብ 90 በመቶ ያህሉ ተሰበሰበ

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል በትግራይ ክልል ቃል ከተገባው ገንዘብ ውስጥ 90 በመቶ ያህሉ ተሰበሰበ፡፡

የክልሉ ህዳሴ ግድብ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃነ ተኸሉ እንዳሉት፣ከክልሉ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 548 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ቃል ተገብቷል፡፡

ህብረተሰቡ ቃል ከገባው ገንዘብ እስካሁን 460 ሚሊዮን ብር ቦንድ በመግዛት ገቢ ማድረጉን አስታውቀዋል።

"በተያዘው ዓመት ለመሰብሰብ ቃል የተገባው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ገቢ ለማድረግ የገቢ አሰባሳቢና የተለያዩ አደረጃጀቶች ተቋቁመው በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው" ብለዋል።
ዘንድሮ ከክልሉ አርሶ አደሮች የ46 ሚሊዮን ብር እንዲሁም 25 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከከተማ ነዋሪዎችና ከንግዱ ማህበረሰብ የቦንድ ግዠ ለመፈጸም ቃል መገባቱን ኃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ መንግስት ሰራተኞች ደግሞ የ10 ሚሊዮን ብር የቦንድ ሽያጭ ለማካሄድ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

"የህዳሴ ግድብ ችቦ ከፊታችን ህዳር ወር ጀምሮ በክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች በመዘዋወር ህብረተሰቡን በማነሳሳት ተሳትፎው እንዲያጠናክር ይደረጋል" ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ በአንድ ወር 80 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ ድጋፍ ያደረገበት ወቅት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ብርሃነ፣"ቀደም ሲል በክልሉ ህዝብ ውስጥ የነበረው እልህና ወኔ እስከ ግድቡ ግንባታ ፍፃሜ ድረስ አጠናክሮ መቀጠል አለበት "ብለዋል።

ባንኮች ቦንዶች አዘጋጅተው በማቅረብና መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ህዝቡን በማነሳሳትና በማበረታታት ያሳዩትን ተነሳሽነት አሁንም አጠናክሮው መቀጠል እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የትግራይ ክልል አርሶ አደሮች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ኃይለሚካኤል ተክሌ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት አባላት የአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግሯዋል።

"የማህበሩ አባል የሆኑ 350 ሺህ አርሶ አደሮች በነብስ ወከፍ ከ50 ብር ጀምሮ ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ግንባታ ያላቸውን ድጋፍ አሳይቷዋል"ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የአባላቱን ቁጥር ወደ ግማሽ ሚሊዮን በማሳደግ በፍላጎታቸው ቦንድ ገዝተው እንዲቆጥቡ ለማድረግ ማህበሩ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም አቶ ኃይለሚካኤል ገልጸዋል።

"ቦንድ መግዛት የአርሶ አደሩ የቁጠባ ባህልን እንዲያሳድግ ለማድረግ የሚያግዝ በመሆኑ ከአንድ ሺህ 500ብር በላይ በፍላጎት ለመቆጠብ የማነሳሳት ስራ ይሰራል "ብለዋል።
ጥቅምት 19/2010/ኢዜአ