ዜና ዜና

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እና የህብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት 11ኛ የጋራ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

በአዲስ አበባ ነገ የሚጀመረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እና የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አፍሪካዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚወያይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢፌዴሪ ቋሚ መልክተኛ አምባሳደር ዶክተር ተቀዳ አለሙ ተናገሩ።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ እና ተለዋጭ አባል ሀገራት ተወካዮች፥ ነገ በሚጀመረው 11ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እና የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባላት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቋሚ መልክተኛ እና የምክር ቤቱ የወቅቱ ሊቀ መንበር አምባሳደር ዶክተር ተቀዳ አለሙ፥ በስብሰባው የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና አጀንዳ ይሆናሉ ብለዋል።

አምባሳደር ዶክተር ተቀዳ ምክር ቤቱ አርብ በሚያካሂደው ዋናው እና መደበኛ ስብሰባው፥ የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ፣ የሶማሊያ ቀውስና የቻድ ተፋሰስ ሃገራት ዋና የትኩረት ነጥቦች እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

የግብፅ አምባሳደር በበኩላቸው፥ አፍሪካውያን በየጊዜው በአህጉሪቱ የሚፈጠሩ ቀውሶች እንዲፈቱ በትጋት መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አምባደሩ ኢትዮጵያ በኢጋድ በኩል ለቀጠናው መረጋጋት የምታካሂደውን ጥረት አድንቀው፥ በነገው ስብሰባም በአህጉሪቷ ውስጥ ለሚካሄዱ የሰላም ማስከበር ስራዎች፥ በፋይናንስ ምንጮች ዙሪያ ትኩረት እንዲሰጥ እንሰራለን ነው ያሉት።

ነገ በሚጀመረው የፀጥታው ምክር ቤት አሜሪካን ወክለው አዲስ አበባ የገቡት አምባሳደር ሚሸል፥ አፍሪካውያን በቀውስ ጊዜ ለዜጎች ደህንነት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአፍሪካ ሀገራት ቀውስ ሲፈጠር በሚደረግ የፍትህ ፍለጋ ወቅት ለችግሩ ተጎጂዎችም ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ነው ያነሱት።

የቻይናው ተወካይ አምባሳደር ጄ በበኩላቸው፥ የአዲስ አበባው ስብሰባ የአፍሪካን ችግር ከምንጩ እንድንረዳው እድልን የፈጠረ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጋራ በመሆን በአህጉሪቷ በየጊዜው ለሚፈጠሩ ቀውሶች መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸውም አንስተዋል።

ነገ በሚጀመረው የምክርቤቱ ስብሰባ ቆይታም አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንመክራለን ይላሉ።

ሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ስብሰባ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት የሩሲያው ተወካይ ደግሞ፥ በየጊዜው የሚፈጠሩ ቀውሶችን በወታደራዊ ሃይል ብቻ ከመፍታት ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን መፈለጉ መልካም መሆኑን አስምረውበታል።

በአዲስ አበባ የሚካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው፥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአለም አቀፍ ድርጅቶች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሙሉጌታ ዘውዴ ይናገራሉ።

አምባሳደር ሙሉጌታ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ስብሰባ ለኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም አስረድተዋል።  አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 1 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)