ዜና ዜና

በሸካ ዞን ለህዳሴው ግድብ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

የሸካ ዞን ላታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ የ32 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እየተዘዋወረ የሚገኘው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በዞኑ ሶስት ወረዳዎቸና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ባደረገው የአምስት ቀናት ቆይታ ነው ድጋፉ የተሰባሰበው፡፡

የዞኑ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ አቶ አድነው አባተ  እንደገለጹት ዋንጫው በዞኑ ሲዘዋወር ከቦንድ ሽያጭ 13 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም የተሰበሰበው ገንዘብ ከሶስት እጥፍ በላይ ደርሷል፡፡

ህብረተሰቡ ከቦንድ ግዥው በተጨማሪ የአይነት ስጦታ ማበርከቱንም ነው ሰብሳቢው የተናገሩት፡፡

ዋንጫው በሸካ ዞን የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ዛሬ ወደ ቤንች ማጂ ዞን ተሸኝቷል።

ዋንጫውን በዞኑ 10 ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር ለ15 ቀናት በማዘዋወር በቦንድ ሽያጭ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን   የዞኑ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሽመልስ መኩሪያ አስታውቀዋል፡፡

በቴፒ ከተማ በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ወልዳይ ገብረመድህን ዋንጫው ወደ ዞኑ መምጣቱን ምክንያት በማድረግ የ10 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

በማሻ ወረዳ ኪዮ ቀበሌ በቡናና ቅመማ ቅመም ልማት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ልኡል ቀለም በበኩላቸው በግላቸው የ150 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

የድርጅቱ ስድስት ቋሚ ሰራተኞችም አንድ ላይ በመሆን የ12 ሺህ ብር ቦንድ ገዝተዋል።

የግድቡ ግንባታ የህዝቦችን አንድነትና ትስስር ያጠናከረ በመሆኑ ስራው እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

ሀዋሳ ነሐሴ 8/2009(ኢዜአ)