ዜና ዜና

የጃፓን መንግስት ለኢትዮጵያ የ50 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አደረገ

ጃፓን ለኢትዮጵያ ለታዳሽ ሃይል ማመንጫ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ለትምህርት ዘርፍ ድጋፍ የሚውል የ50 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አደረገች።

የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታው አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺንቺ ሴይዳ ተፈራርመውታል።

ገንዘቡ በትግራይ ክልል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት፣ የአሉቶ ላንጋኖ የጂኦተርማል የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ለማስፈጸም እና የባሀር ዳር ከተማን የውሃ አገልግሎት ለማሻሻል የሚውል ነው ተብሏል።

በድጋፉ አንደኛው ክፍል በትግራይ ክልል 8 ሺህ 956 ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 7 ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ በክልሉ ገጠራማ አካባቢዎች ያለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሽፋንን ለማሳደግ ይረዳል ነው የተባለው።

ለአሉቶ ላንጋኖ የጂኦተርማል ሃይል ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ በሚለው ድጋፍም፥ ከ3 መቶ ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ከዚህ ባለፈም ድጋፉ የባህር ዳር ከተማን የውሃ አገልግሎት በማሻሻል የከተማዋን ነዋሪ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያግዝ ገንዘብም የተካተተበት ነው።

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 5 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)