ዜና ዜና

የግድቡ ግንባታ አፈፃፀም 60 በመቶ ደረሰ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ አፈፃፀም 60 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።

የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የግድቡን የሲቪል የሃይድሮ እና ኤሌክትሮ መካኒካል የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላም ከሁለቱ ተቋራጭ ኩባንያዎችና አመካሪ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር በአሁኑ ወቅት ግድቡ በደረሰበትና በቀጣይ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ውይይት አድርገዋል።

የግድቡ የሲቪልና መካኒካል ስራ በበጋ ወቅት እንደነበረው አሁንም በክረምት ወቅት መቀጠሉን ዶክተር ደብረፅዮን ጠቁመው የክረምቱን ስራ ልዩ የሚያደርገው የጎርፉን ሁኔታ አስቀድሞ በመገንዘብ በጥንቃቄ እየተሰራበት መሆኑ ነው ብለዋል።

ሰራተኛውና ተቋራጮቹ የግድቡን ስራ በታቀደው ደረጃ በማስኬድ በህዝብና በመንግስት የተጣለባቸውን አደራ በኃላፊነት በመወጣት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ፤ የግድቡ ግንባታ በጥራትና በብቃት እየተከናወነና በአሁኑ ወቅት በዚሁ ፍጥነት ኃይል ወደ ሚያመነጭበት ምዕራፍ በመጠጋት ላይ ነው። '' ኃይል ለማመንጨት አልመን እየሰራን እንደመሆናችን ወደ ቅድመ ኃይል ማመንጨት ለመግባት ስራው በተፋጠነ መልኩ እየተካሄደ ነው'' ሲሉ ዶክተር ደብረፅዮን ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በመንግስት ደረጃ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር በተገለጸው መሰረት ይህን በተግባር መሬት ላይ ለማረጋገጥ ስራው እየተከናወነና እየታየ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 6ኛ ዓመት ባለፈው መጋቢት 27 መከበሩ የሚታወስ ነው።

ሀምሌ 30/2009 /ኢዜአ/