ዜና ዜና

ሃገር አቀፍ 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን ድርድር በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ተስማሙ

ኢህአዴግን ጨምሮ 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን ውይይት በ90 ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ ከስምምነት ላይ ደረሱ።

12ቱ የመደራደሪያ አጀንዳዎችም ባቀረቧቸው ፓርቲዎች ብዛት፣ ለፓርቲዎቹ በቀጥታ ባላቸው ቅርበት እና በድርድሩ ዓላማ መሰረት ቅደም ተከተል እንዲወጣላቸው ተደርጓል።

በዚህም መሰረት የምርጫ ህጎችን አካቶ የያዘው አብይ አጀንዳ በቅድሚያ ድርድር የሚካሄድበት ሆኖ ተመርጧል። 

በዚህ አብይ አጀንዳ ስር የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅና የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር አዋጆችም ተካተዋል።

የፀረ ሽብር፣ የብዙሃን መገናኛ እና የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጆች ደግሞ በአደራዳሪዎቹ በተከታይነት የተቀመጡ መደራደሪያ አጀንዳዎች ናቸው።

የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ተቋማት አደረጃጃትና አፈፃፀም የፍትህ አካላት አደረጃጀት አዋጅና አፈጻፀምም ቀርቧል።

ዜጎች በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው የመስራት መብት እና የክልሎች አሰራር፣ የመሬት ሊዝ አዋጅ፣ የልማት ተነሺዎች ካሳ አከፋፈል፣ የግብር ስርዓት ህግና ብሔራዊ መግባባት ደግሞ የድርደሩ ማሳረጊያዎች ይሆናሉ።

በአደራዳሪዎች በቀረበው የድርድር ቅደም ተከታል ላይ ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሀሳብ አንስተዋል።

መኢህድ፣ ኢራፓ፣ መኢብን እና ቅንጅት የድርድሩ ቀዳሚ አጀንዳ ብሔራዊ መግባባት መሆን አለበት በማለት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የተወሰኑ ፓርቲዎች የተሰነዘረውን ሀሳብ ተከትለው ኢህአዴግ ያቀረበውን ሀሳብ በመቀበላቸው፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ተያያዥ ጉዳዮች የድርድሩ ማስጀመሪያ እንዲሆን ተስማምተዋል። 

ፓርቲዎቹ የጋራ መግባባት ያልደረሱባቸው የአጀንዳ ቅደም ተከተል በድምፅ ብልጫ እንዲወሰን ተደርጓል።

በአደራዳሪዎቹ ተዘጋጅቶ በቀረበው የድርድሩ አጀንዳና የጊዜ ስሌዳ፥ ደርድሩ በ263 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ የሚጠይቅ ቢሆንም ፓርቲዎቹ አልተቀበሉትም።

በመጨረሻም ፓርቲዎቹ ድርድሩ በ90 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ የተስማሙ ሲሆን፥ የአንድ አጀንዳ የድርድር የስብሰባ ጊዜ ከአምስት ቀን እንዳያልፍም ወስነዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጥል ለመደራደር በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ በጽሁፍ ለአደራዳሪው ያስገባሉ የሚለው ሀሳብም፥ በመኢብንና በኢራፓ የፖለቲካ ድርድሩ ሀሳብ በጽሁፍ ብቻ መሆን የለበትም በንግግር ለማቅረብ ዕድል ሊኖር ይገባል የሚል መከራከሪያ ተነስቶበታል።

ኢህአዴግ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚደራደሩበትን አጀንዳ በጽሁፍ ማቅረብ ካልቻሉ ፓርቲው ለተደራዳሪዎች ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገር ገልጿል።

በዚህም ሃገር አቀፍ 16 የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ፥ በአምስት ቀናት ውስጥ መደራደር የሚፈልጉበትን አጀንዳ በጽሁፍ ለአደራደሪዎች እንዲያስገቡ ወስነዋል።

 

በድርድር አጀንዳነት ከፀደቁት መካከል፦ 

• የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ይበኙበታል። 

• የምርጫ ህግ 

• የፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ

በተከታይነት የፀደቁ የመደራደሪያ አጀንዳዎች፦ 

• የፀረ ሽብር ህግ 

• የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት ህግ 

• የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ማደራጃ አዋጅ 

• የታክስ ስርዓት አዋጅ 

• የመሬት ሊዝ አዋጅ እና የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ ሁኔታ በንዑስ የድርድር አጀንዳነት ፀድቀዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም፦ 

• የዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ ተቋማት አደረጃጃት 

• ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመስራትና ሀብት የማፍራት መብት ከክልል መንግስታት ህጎች አንጻር 

• ወቅታዊ እና ኢኮኖሚ ወለድ የህዝብ ጥያቄዎች 

• ብሄራዊ መግባባት 

• የፍትህ ተቋማት አደረጃጀት እና አፈጻጸም አዋጆችም በፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር የፀደቁ አጀንዳዎች ናቸው። 

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)