ዜና ዜና

ኢትዮጵያ በነዳጅ እና በተፈጥሮ ጋዝ ላይ ተስፋ ሰጪ ተግባራትን እየሰራች መሆኗን የኢትዮጵያ የፔትሮሊየም ፈቃድ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

• በአፋር፣በጋምቤላ እና በሶማሌ አካባቢዎች በአምስት ኩባንያዎች ነዳጅ እየተፈለገ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ለማምረት ተስፋ ሰጪ ስራ እየሰራች መሆኗን የኢትዮጵያ የፔትሮሊየም ፈቃድ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ ዳይረክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ቀጸላ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባሳለፍናቸው ጥቂት ወራት ነዳጅ የማምረት ሙከራ ላይ ናት፡፡ ከዚህም በቀን ከ120 እሰከ 130 በርሚል ነዳጅ እየተመረተ መሆኑን የኢትዮጵያ የፔትሮሊየም ፈቃድ አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር ቀጸላ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ከሶስት ጉድጓዶች በቀን 4መቶ 50 በርሚል ነዳጅ ለማምረት ታቅዶ ሲሰራ ነበር፡፡
ይሁን እንጅ ስራው ለጥቂት ጊዜያት እንደተከናወነ እንዲቆም መደረጉን ነው ዶክተር ቀጸላ የገለጹት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ነዳጁን እንዲያከፋፍሉ የተስማሙ ድርጅቶች የንግድ ፈቃድ ስለሚያስፈልጋቸው መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡ በመሆኑም ነዳጁን ላለማባከን ሲባል ምርቱ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል፡፡

የንግድ ፈቃዱን ለማውጣት ከሚመለከተው አካል ጋር እየሰራን መሆኑን እና ይህ እንደተጠናቀቀስራው እንደሚቀጥል ነው ዶክተር ቀጸላ የተናገሩት፡፡
የነዳጅ ምርቱ ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ ቢውል እንኳ ኢትዮጵያ የሚበቃትን ያህል ሳታመርት ለውጭ ሀገራት እንደማትሸጥም ነው ዳይሬክተሩ ያረጋገጡት፡፡
ጥልቅ የነዳጅ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ቀጸላ የነዳጅ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን እና ይህም እስከ ሁለት ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

አምስት የውጭ ሃገር እና የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ነዳጅ ላይ ጥናት እያካሄዱ መሆናቸውን እና ስራው ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ዶክተር ቀጸላ ገልጸዋል፡፡ ከአምስቱ ከባንያዎች መካካል ፖሊ ዲ ሲ ኤል የተባለው የቻይና ኩባንያ እና ኒው አጅ የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ በተፈጥሮ ጋዝ ላይ ትልቅ ስራ እየሰሩ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያው ሳውዝ ኢስት ኢነርጂ የኢትዮጵያ፣ የሩሲያውጋዝ ፕሮም እና የካናዳው አፍሪካን ኦይል ኮርፖሬሽን ኩባንያ በነዳጅ ስራ ላይ ተስፋ ሰጪ ስራ እየሰሩ መሆኑንም ነው የኢትዮጵያ የፔትሮሊየም ፈቃድ አስተዳደር የገለጸው፡፡

በሙከራ ስራው በኦጋዴን፣ በአፋር እሰከ አብያ ሃይቅ ድረስ እና በጋምቤላ ክልል እየተሰራ መሆኑን እና ስራውን በማስፋት በሌሎች ክልሎችም ለመስራት እንቅስቃሴ እተደረገ መሆኑን ዶክተር ቀጸላ አስታውቀዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ጥቅምት 01/2011 ዓ.ም(አብመድ)