ዜና ዜና

ለአደጋ መረጃ ቅርብ የሆነ ህብረተሰብ በመፍጠር አደጋን መቀነስ እንደሚገባ የብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ የዓለም ዓቀፉን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን ዛሬ ‘የአደጋ ስጋት ቅነሳ መረጃና አካታችነት ለዘላቂ ልማት ማዕቀፍ' በሚል መሪ ሐሳብ ለዘጠነኛ ጊዜ አክብሯል።

በእለቱም የአደጋ ስጋት ቅነሳን ከኢንቨስትመንትና ልማት እቅድ ጋር አጣምሮ የያዘ መመሪያን ይፋ አድርጓል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ ብትሆንም "በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ስትፈተን ቆይታለች" ብለዋል።

አደጋ በሰዎች ማህበራዊ ህይወት የሚያደርሰውን እንግልት ለመቀነስና የቅነሳ ተግባሩ ከኢኮኖሚው እድገት ጎን ለጎን እንዲጓዝ አደጋ የሚያስከትሉ ነገሮችን ቀድሞ በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

መመሪያው ሁሉም ሚኒስቴርና አጋር አካላት በአደጋ ስጋት፣ የአደጋ ስራ አመራር ፖሊሲና ስትራቴጂን በተሰጣቸው ስራና ሃላፊነት ስር አካተው እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ተቋማቱ በመመሪያው መሰረት አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ሁኔታዎች በመከላከልና በመተግበር የአደጋ ስጋትን መቀነስ እንደሚያስችልም ገልፀዋል።

የአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ ቢሰራ አገሪቱን ከአደጋ ተጋላጭነት ማዳን እንደሚቻልም በማውሳት።

ላለፉት 30 ዓመታት በላይ የሚከሰቱ አደጋዎችን ከውጭ በሚገኝ እርዳታ ለመቋቋም ጥረት ሲደረግ ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ ሀገሪቷ አደጋን በራሷ መቋቋምና መከላከል እንድትችል ህብረተሰቡ አደጋ የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን የሚረዳበት መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ኮሚሽኑም ሚኒስቴሮችን በማስተባበርና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት አገሪቷ አደጋዎችን ከውጭ እርዳታ ተላቃ በራሷ መቋቋምና መከላከል የምትችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀው የአደጋ ስራ አመራር ፖሊሲና ስትራቴጂ በ2005 ዓ.ም መፅደቁ ይታወሳል።

ኢዜአ ጥቅምት 1/2011