ዜና ዜና

የኢትዮ-ቱኒዝያ ቢዝነስ ፎረም ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ተካሄደ

የኢትዮ-ቱኒዝያ ቢዝነስ ፎረም በትላንትናው እለት ለመጀመሪያ ጊዜ በሸራተን ሆቴል ተካሂዷል።

የኢትዮያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት እና የቱኒዝያ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና የእጅ ጥበባት ማህበር በጋራ በመሆን ከ40 በላይ የሚሆኑ በአገራችን የሚገኙ ኩባኒያዎች እንዲሁም ከ30 በላይ የቱኒዝያ ኩባኒያዎች በፎረሙ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብርሃቱ መለስ ፎረሙ በሁለቱ አገራት ያለውን የንግድ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።

የማኑፋክቸሪንግ፣ ጨርቃጨርቅ እና የቆዳ ምርት ዘርፎች ላይ አገራችን ቅድሚያ የምትሰጥ በመሆኑ በነዚሀ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም የቱኒዝያ ኩባኒያዎች በማደግ ላይ ባለው የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ መዋዕለነዋያቸውን በማፍሰስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተናግረዋል።

የቱኒዝያ ሪፐብሊክ የውጭ ንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ሂቻም ቤን አህመድ በበኩላቸው የቱኒዝያው ልኡክ ለተደረገለት መልካም አቀባበል አመስግነው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ እንደምትሰራ እና በጥምረት በመስራት የሁለቱን አገራት የንግድ ትስስር ማሳደግ እንድሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክትል ፕሬዝዳንት አሰፋ ገብረስላሴ የዚህ አይነት ፎረሞች መካሄድ የጋራ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱን ለማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው የጥምረት ስራዎችን በማካሄድ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሩን ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የኢትዮያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክትል ፕሬዝዳንት አሰፋ ገብረስላሴ እና የቱኒዝያ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና የእጅ ጥበባት ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አብደሳለም ሉኤድ የአገራቱን የንግድ ትስስር ለማጠናከር የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀበቀይ ጽ/ቤት ዘግቧል።

መስከረም30/2011