ዜና ዜና

ማዕከሉ የተሻሻሉ ሦስት የሰብል ዝርያዎችን ለተጠቃሚዎች መልቀቁን አስታወቀ።

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ያገኛቸውን የተሻሻሉ ሦስት የገብስና የስንዴ ዝርያዎች ለተጠቃሚዎች መልቀቁን አስታወቀ፡፡

በምርምር የተገኙት እነዚህ ሁለት የገብሰ እና አንድ የዳቦ ስንዴ ዝሪያዎች በሽታንና ተባይን  ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ናቸው፡፡

የገብስ ዝርያዎቹ "አዶሼ"  እና " ሞአታ "  ስንዴው ደግሞ  "ሲንጃ" የተሰኙ የአካባቢ መጠሪያ ስያሜ የተሰጣቸው መሆኑን በማዕከሉ የብር እና አገዳ ሰብሎች ቡድን መሪና ተመራማሪ አቶ ሚደቅሳ ታምሩ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ዝርያዎቹ በብሔራዊ የዝሪያ አጽዳቂ ኮሚቴ ከተገመገሙ በኋላ ከሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እውቅና አግኝተው መለቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከስድስት እስከ አስር ሁለት ዓመታት በምርምር ላይ የቆዩ ሲሆን የገብስ ዝሪያዎቹ በሄክታር በአማካይ እስከ 51 ኩንታል እንዲሁም የስንዴ ደግሞ  40 ኩንታል ምርት እንደሚሰጡ በተግባር ተረጋግጧል፡፡

በሄክታር የሚገኘው ምርት መጠን ከነባር ዝርያዎች ከ18 እስከ 21 በመቶ ጭማሪ የሚሰጡ ናቸው፡፡

ተመራማሪው እንዳሉት ዝርያዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ውስጥ በማዳቀል የምርምር ሂደት መገኘታቸው ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡

በተለይ" ሞአታ "  የሚባል ስያሜ ያገኘው የቢራ ገብስ ነው፤ የፕሮቲን ይዘቱ ከፍተኛ በመሆኑ ለብቅል ፋብሪካ ግብዓትነት ተፈላጊ ነው ተብሏል፡፡

ዝርያዎቹ  የደጋ ፣ ወይናደጋና ቆላማ ስነ ምህዳር ላለቸው አካባቢዎች ተስማሚ መሆናቸውንም ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡

ማዕከሉ በምግብ እህል ዘርፍ የአሁኖቹን ሳይጨምር 31 የምርምር ውጤቶች ለተጠቃሚው አድርሷል፡፡

ከጊኒር ወረዳ ሞዴል አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሙጂብ አብዱልከሪም በሰጡት አስተያየት በእጃቸው የሚገኘው የገብስ ዝርያ ዝቅተኛ ምርት ከመስጠቱም በላይ በበሽታ ሰለሚጠቃ የልፋታቸውን ያህል ምርት አግኝተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

አሁን የምርምር ማዕከሉ ያወጣውን ዝርያ  የመነሻ ዘር በመቀበል ለማባዛት ፍላጎት እንዳለቸው ጠቁመዋል፡፡

ማዕከሉ በአካባቢያቸው ከአርሶ አደሩ ጋር በማሳ ላይ በሚያደርጉት ምርምር በምርጥ ዘር አጠቃቀምና ሌሎችም የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች አጠቃቀም ላይ ባገኙት እውቀት ምርታማነታቸው እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ ሌላው  የወረዳው አርሶ አደር አቶ መህሙድ ካሚል ናቸው፡፡

የሲናና ምርምር ማዕከል በ1978 ዓ.ም. ከተቋቋመ ወዲህ የአሁኑን ሳይጨምር 65 በምግብ እህል ፣ በጥራጥሬና በእንስሳት መኖ ላይ ያተኮሩ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱም ተመልክቷል፡፡

    ጎባ ነሀሴ 4/2010(ኢዜአ)