ዜና ዜና

የኢንጅነር ስመኘው በቀለን ስራዎች ህያው የሚያደርጉ አሰራሮች ተዘረጉ።

የኢንጅነር ስመኘው በቀለን ስራዎች ህያው የሚያደርጉ አሰራሮች መዘርጋቱን ውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ሞተው እስከተገኙበት ድረስ በግልገል ጊቤ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አንስቶ እስከ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል።

በዚህም ኢንጅነር ስመኘው ለኢትዮጵያ ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንጻር አበርክቷቸውን ህያው ለማድረግ የተለያዩ አሰራሮችን እንደዘረጋ ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በውኃ ኃይል ልማት ምህንድስና ትምህርት ከፍተኛ ውጤት ለሚያስመዘገቡ ተማሪዎች በየጊዜው ሽልማት መስጠት ሚኒስቴሩ ከዘረጋው አሰራር መካከል አንዱ ነው።

‘ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሽልማት' በሚል ስያሜ በውሃ ሐይል ልማት ዙሪያ ሙያዊ ውይይት እና መሰል መድረኮች በየዓመቱ እንደሚዘጋጁ ተገልጿል።

ለዚሁ የመታሰቢያ ስራዎችና የኢንጅነር ስመኘው በቀለን ቤተሰቦች ለመደገፍ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ መዋቀሩንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የተዋቀረው ኮሚቴ  ከውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረተሰብ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፣ ከመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከኢንጅነር ስመኘው በቀለ ቤተሰቦች የተውጣጣ ነው።

የሟች ወገኖችን ለመደገፍ በርካታ ወገኖች መጠየቃቸውን ተከትሎ ፍላጎቶችን በአግባቡ ለማስተናገድ እንዲቻል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የበላይ ጠባቂነት በሟች ልጅና ሌሎች ቤተሰቦች በጋራ የሚንቀሳቀስ የባንክ ሂሳብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጂ ቅርንጫፍ መከፈቱ ተገልጿል።

በዚህም ቤተሰቡን ማገዝ የሚፈልጉ ወገኖች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጂ ቅርንጫፍ የሂሳብ ቁጥር 1000254503812 ስመኘው ቤተሰቦች በሚል ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል፡፡

  አዲስ አበባ ነሃሴ 3/2010(ኢዜአ)