ዜና ዜና

መንግስት በክልሎች ጣልቃ በመግባት የዜጎችን የመኖር ዋስትናና በነፃ የመዘዋወር መብት ማረጋገጥ ይኖርበታል-የፖለቲካ ፓርቲዎች

የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ በመግባት የዜጎችን የመኖር ዋስትናና በነፃ የመዘዋወር መብት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት እንዳለበት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

መንግስት ግጭት በተከሰተባቸው አካበቢዎች የሰው ህይወት ከመጥፋቱና ንብረት ከመውደሙ በፊት ጣልቃ በመግባትና በአገሪቷ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባሉት አደረጃጀቶች ችግሮችን መፍታት እንደሚገባውም አሳስበዋል።

የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፕሬዝዳንት ልጅ መስፍን ሽፈራው እንደገለጹት በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የህዝቡን ሰብዓዊ መብት ሲጥሱና የዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር መብት ሲገፉ የፌዴራል መንግስት ባሉት የተለያዩ መዋቅሮች ችግሩን መፍታት ይገባዋል።

የፌዴራል መንግስት ያለውን ስልጣን ተጠቅሞ ጣልቃ በመግባት ችግር መፍጠር የለበትም በማለት የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ የሰው ህይወትና ንብረት አደጋ ላይ ሲወድቅ ግን አፈጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ምክትል ሊቀምንበር አቶ ገብሩ በርሄ እንደተናገሩት የፌዴራል መንግስት የክልል መንግስታት ጥሪ ካላደረጉለት ጣልቃ መግባት አይችልም የሚል መርህ "ችግር ፈቺ ሳይሆን ችግር ፈጣሪ ነው"።

በመሆኑም የጸጥታ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት የመከላከያ ሰራዊት የህብረተሰቡን ህይወትና ንብረት የሚያድንበት እድል እንዲኖር "ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሰዴፓ) ፕሬዝዳንት ሼክ ሰይድ ይመር በበኩላቸው በክልሎች ችግሮች ሲፈጠር የፌደራል መንግስት የክልል መንግስታት ጥሪ ካላደረጉልኝ አልገባም በሚል መርህ የፌደራል የመከላከያ ሰራዊት በመዘግየቱ በዜጎች ላይ በተፈጠረው ጉዳት ፓርቲያቸው ማዘኑን ገልጸዋል።

መንግስት ለዜጎች ህይወትና ንብረት ቅድሚያ በመስጠት የሚሻሻሉ ህጎች ካሉ በፍጥነት አሻሻሎ ኃላፊነቱን አንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ(ኢዴአን) ሊቀ መንበር ጎሹ ገብረስላሴም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች "በክልል አመራሮች፣ በዞንና በቀበሌ አስተዳደሮችና በታጠቁ ልዩ ኃይሎች ነው" ይላሉ።

ችግር የሚፈጥሩ አካላት ህገ መንግስቱን መተማመኛ ማድረጋቸው ስህተት መሆኑን ጠቁመው የፌዴራል መንግስት የጸጥታ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሰው ህይወት ከመጥፋቱና ንብረት ከመውደሙ በፊት በአፋጣኝ ጣልቃ በመግባት እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ሲሉም ገልጸዋል።

ፓሪቲዎቹ በጅግጅጋ በዜጎች ላይ ለተፈጸመው ድርጊት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ድርጊቱን በጽኑ አውግዘዋል።

 

  አዲስ አበባ ነሃሴ 3/2010 (ኢዜአ)