ዜና ዜና

ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ጋር የአራት ቢሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመች።

ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዲ.ኤፍ.አይ.ዲ) ጋር የ115 ሚሊየን ፓውንድ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመች።

ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ እና የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ተወካይ ወይዘሮ ፔይኒ ሞርዳንት ናቸው።

በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ዶክተር አብርሃም እንዳሉት፤ የገንዘብ ድጋፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን ማዘመን፣ ለአጠቃላይ ምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ ለኢንዱስትሪ ሽግግር እና ለስደተኞች ድጋፍ የሚውል ነው።

የሚደረገው ድጋፍ መንግሥት ምጣኔ ሀብቱን በፍጥነት ለማሳድግና ኢንዱስትሪውን ለማስፋት ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የጎረቤት አገሮች ስደተኞች ያሉባት አገር በመሆኗ ለመፍጠር ከታሰበው መቶ ሺህ የሥራ ዕድል ውስጥ ሰላሳ  ሺህ የሚሆነው ለስደተኞቹ መሆኑን ጠቁመዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራው የአገሪቱን የኢንዱስትሪ ዕድገት ለማገዝ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አብርሃም መርሃ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ 80 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በድጋፍ ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ 35 ሚሊዮን ፓውንድ የታክስ ሥርዓቱን ለማዘመን እንደሚውል ገልጸው የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን ማዘመን ዘላቂ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ንግድና ኢንቨስትመንትም ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የእንግሊዝ መንግሥት ለሚያደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ ትልቅ አድናቆት እንዳለው ዶክተር አብርሃም ገልጸዋል።

የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ተወካይ ወይዘሮ ፔይኒ ሞርዳንት በበኩላቸው ድርጅቱ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን የሚያግዙ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው በቀጣይ የሥራ ዕድል ፈጠራን ጨምሮ የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎችን የመደገፍ ተግባሩን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የልማት ድጋፎችን ሲያደርግ የቆየ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።

 

  አዲስ አበባ ነሃሴ 2/2010 (ኢዜአ)