ዜና ዜና

ሀገራዊ የካዳስተር ስርአትን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው- የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር

ሀገራዊ የካዳስተር ስርአትን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስትር አስታወቀ።

የመሬት መረጃ አያያዝ ስርአት ዘመናዊ ባለመሆኑ ምክንያት በርካቶች ከቤት እና መሬት ባለቤትነት ውጭ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው።

ለበርካታ አመታት የመንግስት ግብር ሲከፍሉ የነበሩ ሰዎች ይዞታ የተሰራለትን መሬት የባለቤትነት መረጃቸውን በአግባቡ ባለመያዘቸው የእነሱ ባለቤትነት ቀርቶ ለሌላ ተላልፎ የተሰጠባቸው እንዳሉ ይገለፃል።

ይህን መሰል ችግሮች የከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስቴር የካዳስተር ስርአት ወይም ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርአትን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርግ ምክንያት ሆኖታል።

የካዳስተር ስርአት የመሬት መረጃን በወረቀት ላይ ሳይሆን በዘመናዊ ስርዓት በኮምፒዩተር ሲስተም እንዲገባ ማድረግ ነው።

ከዚህ ቀደም ሰርአቱን ወደ ትግበራ ለማስገባት ስራዎች እንደተከናወኑ ቢገለፅም ወደ ትግበራ ለማስገባት ግን የተለያዩ እንቅፋቶች እንደነበሩ ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቀዋል።

በዚህም በተለያዩ የክልል ከተሞች ባለፈው አመት ወደ ሙከራ ትግበራ ይገባል ቢባልም ወደ ተግባር መግባት እንዳልተቻለ አንስተዋል።

ሚኒስትሩ፥ ስርአቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ትግበራ ለማስገባት መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ የመሬት መረጃ የሚሰበሰብበት ፕሮግራም ያለው ስርዓትን የማልማት ስራም እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርአት ተግባራዊ በሚደረግበት በሁለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 91 ከተሞች በስርአቱ ትስስር እንደሚፈጠርላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።


በመሆኑም በመስሪያ ቤቱ የሚገኙ ባለድርሻዎች የመፈፀም ብቃታቸውን ማሳደግ እና ከስርዓቱ ጋር ማዋሃድ ከሚያስፈልጉት መሰረተ ልማቶች ተነጥሎ የሚታይ አለመሆኑን አቶ ጃንጥራር አባይ አስታውቀዋል።

ስርአቱ በአዲስ አበባ በሙከራ ደረጃ ላይ ቢሆን በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን፥ በአንዳንድ ከተሞች ላይ በጅምር መሆኑን አንስተዋል።

ሆኖም በጅምር ላይ የሚገኙት እነዚህ ስራዎች ሚኒስቴሩ ከያዘው እቅድ አኳያ ውጤታማ እንዳልሆኑና ወደ ኋላ የቀሩ መሆናቸውን አቶ ጃንጥራ ገልፀዋል።

በመሆኑም የካዳስተር ስርአቱ በሚፈለገው ደረጃ ወደ ትግበራ ለማስገባት፣ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እና የመሬት መረጃን ዘመናዊ በማድረግ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍም ሀገራዊ የመረጃ ሰርአቱ የሚተሳሰርበት መሰረተ ልማት የማልማት ሰራዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል።

ሚኒስትሩ ይህ ሀገራዊ የመረጃ ሰርአት ቋት የማልማት ስራ ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል ።

በተለይ በ2011 በጀት አመት ጥሩ በሚባል እና ውጤታማ በሆነ መንገድ በርካታ ከተሞች በስርአቱ የሚተሳሰሩበት ስራ ለማከናወንም ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ይህም የመሬት መረጃ አያያዝ ሰርአትን ከማዘመን በተጨማሪ የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በመፍታት በኩል ትልቅ መፍትሄ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት ሲሉ አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል።

 አዲስ አበባ፣ነሀሴ 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)