ዜና ዜና

በምስራቅ ሸዋ ዞን 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመስኖ ልማት ለማግኘት እየተሰራ ነው

በሁለተኛው ዙር መስኖ ልማት 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የምስራቅ ሸዋ ዞን መስኖ ልማት ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ሚደቅሳ የመስኖ ልማቱ ስራ እየተካሄደ ያለው በዞኑ 10 ወረዳዎች ውስጥ ነው።

የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ፣ ዘመናዊና ባህላዊ መስኖ እንዲሁም ኩሬና በእጅ በሚሰሩ የጉድጓድ ውሃ በመጠቀም 57 ሺህ ሔክታር መሬት እየለማ ይገኛል።

ከሚለማው መሬት 90 በመቶ ቲማቲም፣ቀይ ሽንኩርት፣ቃሪያ፣ሃባብ፣ ፎሶሊያና ጥቅል ጎመን ሲሆን ቀሪው በጥራጥሬ፣ቦቆሎና ስንዴ ሰብል የተሸፈነ ነው።

በልማቱ ላይ 47 ሺህ 439 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ከመካከላቸውም 8 ሺህ 287 ሴቶች ናቸው።

አርሶ አደሮቹ ጥራት ያለው ምርት አምርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በየደረጃው የተመደቡ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በአቅራቢያቸው የሙያ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውንም አቶ ጌትነት ጠቅሰዋል።

ከመስኖ ልማቱም 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል።

ስራ አስኪያጁ እንዳመለከቱት በምስራቅ ሸዋ በብዛት ለሚመረተው የአትክልት ምርት በአፋጣኝ ገበያ ማግኘት ካልተቻለ በቀላሉ ለብልሽት ተዳርጎ በአምራቹ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቷል።

እስከ አሁንም በኦሮሚያ፣ትግራይ፣ሐረር፣ሶማሌና አፋር ክልል ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣መሰረታዊ ኀብረት ስራ ማህበራትና ከባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ዩኒዬን ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በዞኑ አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ የዶድቻ መስኖ ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አዩብ በዳሶ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መንግስት በገነባው ዘመናዊ መስኖ ፕሮጀክት 164 የማህበሩ አባላት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የማህበሩ አባላት በዘንድሮ የመጀመሪያው ዙር መስኖ በ67 ሄክታር መሬት ላይ ፎስሊያ፣ቲማቲም፣ቀይ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን በማልማት 8 ሺህ 556 ኩንታል ምርት አግኝተዋል፡፡

ምርቱን ለመቂ ባቱ የገበሬዎች ኀብረት ሥራ ዩኒዬንና ለነጋዴዎች በማስረከብ ባገኙት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በ1994 ዓ.ም 119 አባላትን በማቀፍ በ50 ሺህ ብር ካፒታል የተመሰረተው ማህበሩ ዛሬ ላይ ካፒታሉን ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አድርሷል።

እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ የአባላቱም ዓመታዊ ገቢ ከ100 ሺህ እስከ 150 ሺህ ብር ነው።

በምስራቅ ሸዋ ዞን በመጀመሪያው ዙር 75 ሺህ ሄክታር መሬትን በመስኖ በማልማት ከ16 ነጥብ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የዞኑ መስኖ ልማት ባለሥልጣን አመልክቷል፡፡

አዳማ ግንቦት 9/2009/ኢዜአ/