ዜና ዜና

ግድቡ የኢንጂነር ስመኘው ስምና ታላቅ ስራ የሚዘከርበት ይሆናል – የህዳሴው ግድብ ሰራተኞች

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የኢንጂነር ስመኘው ስምና ታላቅ ስራ የሚዘከርበት እንደሚሆን የግድቡ ሰራተኞች ገለጹ።

የፕሮጀክቱ ሰራተኞች በትናንትናው ዕለት በግድቡ የጧፍ ማብራት ስነ-ስርዓት አካሂደዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም መስቀል አደባባይ በመኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው የሚታወስ ነው።

የፕሮጀክቱ ሰራተኞች በኢንጂነር ስመኘው ሞት ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በእርሳቸው መሪነት በመከናወን ላይ የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ስማቸውና ታላቅ ስራቸው የሚዘከርበት ይሆናልም ነው ያሉት።

ኢንጂነር ስመኘው ሞተ የሚባለው የግድቡ ግንባታ ሲጓተት አልያም ሲቆም ነው ያሉት ሰራተኞቹ እስከ ግንባታው ፍጻሜ በትጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ስርዓተ-ቀብር ዛሬ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በተገኘበት ተፈጽሟል።

 አዲስ አበባ ሃምሌ 22/2010(ኢዜአ)