ዜና ዜና

ጋህአዴን የኢትዮ- ኤርትራን ስምምነት እንደሚደግፍ አስታወቀ።

ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮ- ኤርትራ ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት ወደ ቀድሞው ለመመለስ መንግስት ያካሄደውን የሰላም ስምምነት እንደሚደግፈው የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋህአዴን/ አስታወቀ።

በሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየመጡ ያሉትን ሁለንተናዊ ለውጣች ቀጣይነት ለማረጋገጥ ንቅናቄው ጠንክሮ እንደሚሰራም ገልጿል።

የጋህአዴን ጽህፍት ቤት ኃላፊና የመንግስት ተጠሪ አቶ ኡኩኝ ኡቡያ ለኢዜአ እንደገለጹት በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ወደ ቀድሞው ለመመለስ በሀገራቱ መሪዎች የተደረሰው ስምምነት የሚደነቅ ነው።

የተደረሰው ስምምነት ተነፋፍቀው የነበሩ የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነታቸውንና ሰላምን በማጠናከር ለሀገራቱ እድገት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ያለማንም የአደራዳሪ የሰላም ስምምነቱን መፈጸማቸው የአመራር ብስለትነታቸውን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የዓለም ሀገራት ምሳሌና ተሞክሮ የሚሆን ተግባር ጭምር እንደሆነም ገልጸዋል።

የተደረሰውን የሁለቱን ሀገራት የሰላም ስምምነት የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ / ጋህአዴን / ከልብ እንደሚደግፈውና ለተግባራዊቱን እንደሚሰራ ተናግረዋል።

መንግስት የልማት ድርጅቶችን አብዛኛውን ድርሻ በመያዝ ለግል ባለአክሲዮኖች እንዲሸጡ የወሰደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋህአዴን ያመነበት ውሳኔ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሀገሪቱ እየመጡ ያሉትን ሁለንተናዊ ለውጦች ዳር ለማድረስም ጋህአዴን አባላቱንና ህዝቡን አስተባብሮ  በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በሀገሪቱ እየታዩ ያሉትን ለውጦች ወዳ ኋላ ለመቀልበስ የሚሞክሩ ጥቂት ፀረ-ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ ጋህአዴን በጽናት እንደሚታገል አቶ ኡኩኝ አስገንዝበዋል።

 ጋምቤላ ሀምሌ 4/2010(ኢዜአ)