ዜና ዜና

ጨፌ ኦሮሚያ የአስራ አንድ ዳኞችን ሹመት አነሳ

ጨፌ ኦሮሚያ በስነ ምግባር ጥሰት ምክንያት የአስራ አንድ ዳኞችን ሹመት አነሳ።

ጨፌው ከባድና ቀላል የስነ ምግባር ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው ካቀረቡለት 326 ዳኞች መካከል 11 በተለያዩ ወረዳዎች ይሰሩ የነበሩ ዳኞች እንዲሰናበቱ ወስኗል።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2010 በጀት አመት አፈጻጸሙን ለጨፌው አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ደሳ ቡልቻ ሪፖርቱን ባቀረቡበተ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ 116 ዳኞች ቀላል የስነ  ምግባር ጥሰት ፈጽመው በመገኘታቸው በማስጠንቀቂያ ታልፈዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከባድ የስነ ምግባር ጥሰት ፈጽመው የተገኙ 210 ዳኞች እንደየጥፋታቸው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የደመወዝ ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡

አስራ አንድ ዳኞች ግን በሙሰና፣ ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በማሳየት፣ስራ ላይ ባለመገኘትና ህግን ተላልፎ ውሳኔ በመስጠት ጥፋተኛ መሆናቸው መረጋገጡን ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

በዚሁ መሰረት ጨፌው ዳኞቹ ከሰራ እንዲሰናበቱ ወስናል።

በሌላ በኩል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት በበጀት ዓመቱ ከታዩት ከ600 ሺህ በላይ ክሶች ውስጥ ከ570 ሺህ በላይ መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተሰጡ የህግ አገልግሎቶች 88 ሚሊየን ብር ለመንግስት ገቢ የተደረገ ሲሆን ለ89 ሺህ ሰዎች ነጻ የሕግ አገልግሎት ተሰጥጥቷል ብለዋል።

የጨፌው አባላት በበኩላቸው በከባድ የስነ ምግባር ጥሰት የተሰናበቱ ዳኞች በቀጣይ ጠበቃ ሆነው የሚሰሩ በመሆኑ ዳኞች በህግ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አባላቱ የሐሰት ምስክርነት አሁንም በስፋት አየተስተዋለ የሚገኝ ችግር መሆኑን ጠቅሰው ሕብረተሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው እምነት የጠነከረ እንዲሆን ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ፍርድ ቤቶች ከአድልዎ፣ ሙስናና ብልሹ አሰራራ በጸዳ መልኩ አገልግሎት የሚሰጡበት አግባብ ሊመቻች እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ጨፌው በከሰዓት ቆይታው በክልሉ ዋና ኦዲተር አፋጻጸም ላይ ይወያያል።

ሐምሌ 3/2010/ኢዜአ/